Blog Archive

Thursday, August 17, 2017

የእመቤታችን ስሞችና የአማርኛ ትርጉማቸው

የእመቤታችን ስሞችና የአማርኛ ትርጉማቸው


ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት

“ሰላም ለክሙ አርድእተ ልሣነ ግእዝ ኵልክሙ ዮም እተረጉም ለክሙ ስማ አው አስማቲሃ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል በክልኤ ማርያም”




በዛሬው ዝግጅታችን ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስሞች በከፊል እንማራለን ። እንደሚታወቀው የተለያዩ የግእዝ ቃላትን ለማጥናት አልፎ አልፎ በማኅበራዊና በመንፈሳዊ ሕይወት ዙሪያ አርእስትን እየመረጥን እንደ ምንማር ተነጋግረናል፡ ባለፈው በማኅበራዊ ዙሪያ ስለ ተውኔትና ተዋንያን ተመልክተን ነበር ዛሬ ደግሞ በመንፈሳዊው ዙሪያ እንመለከታለን ማለት ነው። ስለ እመቤታችን ስሞች ዛሬ እንድንማር የመረጥኩበት ምክንያት።

1ኛ የእመቤታችን ስሞች ከግእዝ ቃላት በብዛት በሁለት ቃላት የተቀነባበሩና ተናባቢ ቃላትን ፤ የምን እና የማን የሚሉትን ባለቤትነትን የሚያመለክቱ ሆሄያትን የምናውቅባቸው  ናቸው ስለዚህ ቃላትን ልንማርባቸው ስለምንችል ነው
2ኛው በአሁኑ ወቅት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ ጾም የሆነው ጾመ ፍልሰታ ስለሆነ በረከትን የምናገኝበት በመሆኑ የእመቤታንን ስሞች መረጥኩ ማለት ነው።

እመቤታችን የምትጠራባቸው ስሞች በጣም ብዙዎች ስለሆኑ ሁሉንም ማጠቃለል ስለማይቻል የተወሰኑትን ማለትም ተዘውትረው የሚጠሩትን ብቻ ባጭሩ እንመለከታለን። ለወደፊቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በተመለከተ ሰፊና ተከታታይ ትምህርት ይኖረናል።

ስም የሚለው ቃል በግእዝም በአማርኛም አንድ ነው። ሲበዛ ግን አማርኛው፤ “ስሞች” ግእዙ ደግሞ “አስማት” ይሆናል። ስም የአንድ ነገር፤ አካል፤ ሁኔታ፤ ወዘተርፈ መጠሪያ ማለት ነው።

አብዛኛውን ጊዜ በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ በአገራችን ጭምር ስም እንዲሁ ለመጠሪያ ብቻ አይሰየምም፤ ነገር ግን ስም ሥራን፤ ባሕርይን፤ ዓይነትን፤ ሁኔታን፤ ክስተትን መሰረት በማድረግ ይሰየማል። በመሆኑም የእመቤታችንም ስሞች ማንነቷን፤ ሥራዋን፤ ምርጫዋን፤ ወዘተ መሠረት ያደረጉና የሚገልጡ ገላጮች ናቸው።

ስም ብቻውን ብዙ ነገገርን ይሠራል። ባለ ስሙ እንኳን በአካል ሳይኖር ብቻውን ብዙ ጥቅምን ይሰጣል። ለምሣሌ
“በእንተ ስማ ለማርያም” ወይም (ስለ እመ ብርሃን”) ማለት  “ስለ ማርያም ስም” ስለ ብርሃን እናት ስም ማለት ነው። “ስለ ማርያም ስም” ማለት ነው እንጂ ስሟ እንኳን በግልጽ አልተጠቀሰም። ነገር ግን  በዚህ ዐ/ነገር ብቻ አስደናቂ ሥራ ይሠራል። ምክንያቱም የእመቤታችን  ስም ተወዳጅ ፤ የሚፈራ፤ የሚከበር፤የሚናፈቅም ስም ስለ ሆነ ነው።

በዚህ ቃል ብቻ ሕይወታቸውን እየመሩ ነው የቤተ ክርስቲያናችን  ሊቃውንት ካህናት፤ የሀገርና የሕዝብ መመኪያዎች መምህራን፤ የአገራችንን ታሪክ ከምንጩ በብራና በእንስሳት ቆዳ በእጃቸው እየጻፉ ጥራቱን እንደ ጠበቀ ለትውልድ እንዲቆይ ያደረጉት። 

የዜማ፤የቅኔ፤የመጻሕፍት ትርጓሜ ሊቃውንት የሚማሩት በዚህ ስም ብቻ ነው። ይህንን ዐ/ነገር በመናገር ብቻ ነው። አስደናቂውንና ለወገን መመኪያ ከአምላክ ጋር መነናገሪያ መንፈሳዊ ቋንቋ የሆነውን መንፈሳዊ ትምህርት የተማሩት የእመቤታንን ስም በመጥራት ብቻ ነው። በተለይ በኢትዮጵያውያን መካከል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስም ልዩ ኃይል አለው። ማንም የእሷን ስም ጠርቶ ባዶ እጁን አይመለስም ። በገጠሩ ኅብረተ ሰብ ተማሪ “በእንተ ስማ ለማርያም” ካለ እንጀራ እንኳን ባይኖራቸው ለዘር ተብሎ ተደብቆ ከተቀመጠው እህል ቀንሰው ይሰጣሉ እንንጅ የለንም አይሉ። እና የእመቤታችን ስም ለተራቡት ምግብን፤ ለታረዙት ልብስን፤ ለተቸገሩት መጽናናትን ይሰጣል።

ከብዙ ዎቹ መካከል ከእመቤታችን ስሞች መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው እና እነዚህን በ2ቱ የጾመ ፍልሰታ ቀናት ምሣሌ 14ቱን ብቻ እንመለከታለን።

1.      ማርያም (ማር+ያም=) (ማ=ማኅደረ መለኮት፤ ር= ርግብ፤ ያ=ያንቅአዱ ኀቤኪ፤ ም= ምስአል ወምስጋድ፤)
2.     ድንግል (ቅጽል) (አምላክን ከመውለዷ በፊት፤ በወለደች ጊዜ፤ ከወለደችውም በኋላ) በሐሣቧ፤በሥራዋም ድንግል ናት
3.     ቅድስተ ቅዱሳን(ቀደሰ)(ቅጽል)
4.     እመ ብርሃን
5.     እመ አምላክ
6.     እመ ክርስቶስ
7.     ርኅርኅተ(ቅጽል) ልብ
8.     ሰአሊተ(ቅጽል) ምሕረት(ሰአለ)
9.     ጽንሰታ(ስም) ለማርያም (ጸንሰ)
10.    ልደታ(ስም) ለማርያም(ወለደ)
11.     በዓታ (ስም) ለማርያም(ቦአ)
12.    አስተርእዮታ(ንዑስ አንቀጽ)  ለማርያም(አስተርአየ)
13.    ፍልሰታ ለማርያም (ፍልሰተ ሥጋሃ ለማርያም
14.    ትንሣኤሃ(ስም/ጥሬ ዘር) ለማርያም(ተንሥአ)
15.    ዕርገታ (ስም/ሳቢ ዘር) ለማርያም(አርገ)

ልዑል አምላክ ማስተዋሉን ያድለን
ከአውደ ጥናት ዘግእዝ

በመ/ር መላኩ አስማማው ቢሰጠኝ

No comments:

Post a Comment