Blog Archive

Monday, April 13, 2015

The Resurrection of Christ/የክርስቶስ ትንሣኤ

The Resurrection of Christ/የክርስቶስ ትንሣኤ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን


እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሣኤ በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን።

“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በአቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሠሮ ለሰይጣን፤ አግአዞ ለአዳም፤ እምይእዜሰ ኮነ ፍስሐ ወሰላም።

ይህ ቃል በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ከርስቶስ ከተነሣባት ቅጽበት ዕለተ ዕሁድ ጀምሮ እስከ ርደተ መንፈስ ቅዱስ ወይም መንፈስ ቅዱስን ለዓለም ወይም ለቅዱሳን ሐዋርያት እስከ ላከባት ዕለት ዕለተ-እሁድ ድረስ ለሃምሳ ቀናት የጸሎት ሁሉ መጀመሪያና ማጠቃለያ፤ የሰላምታም መለዋወጫ መጀመሪያም እየሆነ የሚነገር የድኅነት፤ የነጻነት፤ የድል፤ የሰላምና የደስታ አዋጅ ነው።
 ወደ አማርኛ ተብራርቶ ሲተረጎም

·         ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና በጽኑ ሥልጣን ከሞት ተነሣ፤
·         ሰይጣን የተባለ ዲያብሎስን በማይፈታ ጽኑ ሥልጣን አሠረው፤
·         አዳምንም/ወይም የሰውን ዘር ሁሉ ከዘላለም ሞት አድኖ ነጻ አወጣው፤
·         ስለዚህ ማለትም (ክርስቶስ በሞቱ ኃጢአታችንን ደምሥሶ፤ ዲያብሎስን በሰው ልጅ ላይ ከነበረው ሥልጣኑ ሽሮ፤ ሰውንም ከዲያብሎስ ተገኝነት ነጻ ስላወጣው ከዛሬ ጀምሮ ደስታና ሰላም ለሰብ አዊ ፍጡር ሁሉ ሆነ ። ማለት ነው።

አምላካችን እግዚአብሔር እንደኛ ጥበብ ወይም ደግነት ሳይሆን እንደ ቸርነቱ ብቻ ይህቺን ጊዜ ከሕይወታችን ተጨማሪ አድርጎ በነጻ በመስጠት በሕይወት ጠብቆ ይህንን ታላቅ ዕለት እንድናይና የቅዱሱ ታሪክ ተካፋዮች እንድንሆን ስለፈቀደልን የተመሰገነ ነው። አሁንም በማያልቀው ልግሥናው የንስሐ ጊዜን ጨምሮልን የዛሬ አመትም በሕይወት አቆይቶን ችርነቱን እንድናወራ ፈቃዱ ይሁንልን።

“--ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም--” ሉቃ.24፡5

ይህ ዕለት ለክርስትናው ዓለም ሁሉ ታላቁ ቀን ነው። ምክንያቱም የ5500 ዘመን የድኅነተ ዓለም ተስፋ ፍጻሜ ያገኘበት፤ ዕለት ስለሆነ፤ ከሥነ ፍጥረት ሁሉ በተለየ መልኩ ልዩ ሆኖ የተፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር ከወደቀበት፤ የተነሣበት፤ ከሞት ወደ ሕይወት የተመለሰበት፤ ከ5500 ዘመን ለዲያብሎስ ተገዥነቱ ነጻ የወጣበት፤ በአጠቃላይ በአንድ አረፍተ ነገር ሲገለጥ ሰብ አዊ ፍጡር ከአምላኩና ከአባቱ ጋር ታርቆ እንደገና የልጅነት መብቱ ተመልሶለት የወራሽነት መብቱ የተረጋገጠበት ዕለት ነው።

ይህ ዕለት ይህ ዘመን፤ ይህ ታሪክ፤ ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ 3ኛው የታሪክ ምዕራፍ ነው፡
አንደኛው የታሪክ ምእራፍ አምላኩን መስሎ በክብርና በታላቅ እንክብካቤ በገነት ለ7 ዓመታት ያሳለፈው የደስታና የሰላም ታሪክ ነው
ሁለተኛው ምዕራፍ ከወደቀባት ዕለት ጀምሮ ለ5500 ዘመናት ያሳለፈው የትካዜና የሞት፤ የምርኮም ታሪክ ነበር
የዛሬው ሦስተኛው የታሪክ ምዕራፍ ደግሞ የድኅነት ተስፋ፤ የድኅነት ሥራ በድል ተጠቃሎ ወደ ቀደመ ክብሩ የተመለሰበት የድል፤ የደስታና የሰላም ምዕራፍ ሲሆን ይህ የታሪክ ምዕራፍ ከዛሬ 2007(ሁለት ሺህ ሰባት )ዓመታት በፊት የተጀመረ ምዕራፍ ነው። ለዚህም ዓመተ ምሕረት፤ ዓመተ ሰላም፤ ዓመተ ድኅነትም ይባላል። (ይህም የአምላክ የሥጋዌው ዘመን ማለት ነው)

በዚህ ትምህርታችን የሚከተሉትን አርእስት ጠቅለል ባለመልኩ አጠር አጠር አድርገን እንመለከታለን።
ትንሣኤ ምን ማለት ነው?

ትንሣኤ፡ ተንሥአ ተነሣ ከሚለው የግእዝ ግሥ የሚወጣ ስም ሲሆን “ጥሬ ዘር” በመባል ይታወቃል። ወደ አማርኛ ሲተረጎም “መነሣት” ማለት ነው። ምን ዓይነት መነሣት ሲባል፡ በቋንቋነቱ  ብዙ ዓይነት ትርጉሞች አሉት ከጥቂቶቹም መካከል

ከመቀመጫ መነሣት፤
ከእንቅልፍ መነሣት፤
ከሥልጣን መነሣት
ከሞት መነሳት
የመሳሰሉትን ትርጎሞች ሁሉ ሊሰጥ ይችላል ወይም ለመሳሰሉት ሁሉ ልንጠቀምበት እንችላለን።

ከሞት መነሣት የሚለው ወይም የዛሬውን ትምህርታችንን የሚመለከተው ፍች ግን ትንሣኤ ወይም መነሣት ሲባል
ነፍስና ሥጋ በሞተ ሥጋ ምክንያት ተለያይተው “ነፍስ” ወዳስገኛት ወደ እግዚአብሔር፤ ሥጋም ወደ ተገኘበት ወደ መሬት ወይም ወደ መቃብር ከሄዱ በኋላ እንደ ገና በአንድነት ሕያው ሆነወ በአንድ አካል በሕያውነት የመነሣቱ ሂደት ነው “ትንሣኤ” ወይም መነሣት፤ ወይም የሙታን መነሣት የሚባለው።

እንደ ሚታወቀው ወይም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ፈጣሪ ፤ ሥጋ ደግሞ ወደ ተገኘበት ወደ አፈር ወይም ወደ መቃብር ይሄዳሉ።

--“አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።--” መክብብ 12፡7
ስለዚህ በዚህ ትምህርታችን ትንሣኤ የሚለው ቃል ትርጉም ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ከቆዩ በኋላ እንደ ገና በውሕደት መነሣት ማለት ነው።

ትንሣኤ በብሉይ ኪዳን፡

ስለትንሣኤ ሙታን በብሉይ ኪዳን የተገለጸ ሲሆን ስለ ክርስቶስ ትንሣኤና በአጠቃላይም ስለ ሰብአዊ ፍጡር ከሞት በኋላ መነሣትን በተመለከተ ይናገራል።ለምሳሌም ስለ ትንሳኤ ሙታን ከተናገሩት ነቢያት መካከል እነ ነቢዩ ዳዊት፤ ኢሳይያስ፤ ዳንኤል ይገኙበታል። መዝሙር፡ 15÷9 ኢሳያስ፡26÷19 ዳንኤል፡12÷2

 መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በዚህ ዓለም እያስተማረ በሚመላለስበት ጊዜ ትንሣኤን የማያምኑ ሰዱቃውያን በጠየቁት ጊዜ ስለትንሣኤ ብሉይ ኪዳንን እየጠቀሰ አስተምሯቸዋል። ማቴ፡22÷23 በመሆኑም የትንሣኤ ትምህርት በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የተነገረ ወይም የተደገፈ ነው ማለት ነው።

የክርስቶስ ትንሣኤ፡

·         የመድኃኔ ዓለም የአዳኝነት ሥራው ማጠቃለያ
·         ክርስቶስ ሞትንና መቃብርን፤ ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ድል አድርጎ ያሸነፈበት  የድል፤የደሥታና የምሥራች መታሰቢያ ነው(ዕለት ነው)
·         ለሰብ አዊ ፍጡር ሁሉ ለመነሣቱ ማረጋገጫና የተስፋ መሠረት ነው።
በዚህ ጊዜያዊ ዓለም ያለው አድካሚ ህይወት ሁሉ፤ እንደሚያልፍ፤ እያንዳንዳችን ከሞተ ሥጋ በኋል እንደገና ተነሥተን ለዘላለም እንኖራለን ብለን ተስፋ ለምናደርገው ትንሣኤ ሙታን መተማመኛችንና ማረጋገጫችንም ነው፤፡

ክርስቶስ እንዴት እና መቸ ተነሣ።

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ መለኮታዊ ሕይወቱን በቀራንዮ አደባባይ በመሥቀል ላይ በፈቃዱ ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ። ዮሴፍና ኒቆዲሞስን ቅዱስ ሥጋውን በአዲስ መቃብር አሳረፉት ። በአካለ ነፍስ ወደሲኦል ወርዶ ሲኦልን በረበራት ባዶዋንም አስቀራት። በኃጢአት የታሠሩት ሁሉ ተፈቱ የነጻነትን ድምጽ ሰሙ፤ነጻነትንም ተቀዳጁ።

ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥  በእርሱም ደግሞ ሄዶ በወኅኒ ለነበሩ ነፍሳት ሰበከላቸው፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3፡18-19

የክርስቶስ መከራና ሞት በፈቃዱ የተከናወነ ቢሆንም ቅሉ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን  ምክንያት ነበሩ።ምክንያቱም ኢፍትሃዊና ኢሃይማኖታዊ የሆነውን መጥፎ ሥራቸውን በይፋ እያጋለጠ ይወቅሳቸው ስለነበረ በመቀኝነትና በተንኮል፤ በቅንአትም፤ ተነሣስተው ያደረጉት ነው።  ይህንን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ግን ረክተው፤ ተደስተው ተረጋግተውና ተዝናንተው ከተኙ በኋላ  አንድ አስደንጋጭ ነገር ትዝ አላቸውና ህሊናቸውን አናጋው። ይኸውም  ክርስቶስ ስለራሱ ትንሣኤ አስቀድሞ የተናገረው ትንቢት ነበር። ስለዚህ ከእንቅልፋቸው እየባነኑ ተጠራርተው ወደ ገዡ ወደ ጲላጦስ እየገሠገሱ ሄዱ።

 “---በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና። 
ጌታ ሆይ፥ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።  እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። 
 ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው።  እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ---”። ማቴ.27፡62-66

የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ከጥበቃ ክፍሎች ጋር በመሆን መቃብሩን በታላቅ ድንጋይ በጥንቃቄ አተሙት፤ኃያላን የሆኑ ጥባቂዎችንም መርጠው በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ በታላቅ ድንጋይ በታተመው መቃብ ዙሪያ አሰለፉ።

ነገርግን “ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም” በማለት ስለሕያው ቃሉ ተፈጻሚነት የተናገረው መድኃኔ አለም የተናገራት አንዲት ቃል እንኳን ስለማትወድቅ እንደ ተናገረው ከተወሰነቺው ጊዜ ቅጽበት እንኳን ሳታልፍ በሦስተኛው ቀን ተነሣ። የታተመው ድንጋይም ሆነ በተጠንቀቅ የቆሙት ኃያላን ወታደሮች ምንም ኃይል አልነበራቸውም። ኃይላቸው ደከመ፤ ጆሮቻቸው መስማት ተሳናቸው፤ ዓይኖቻቸው ማየትን አቆሙ።

በመሆኑም መቃብሩ ባዶ ሆኖ ተገኘ፤ ቅዱሳን መላእክትም ከሰማያት ወርደው “ሕያውን ከሙታን ለምን ትፈልጉታላችሁ”? በዚህ የለም፤ እንደተናገረ ተነሥቷል። በማለት መሰከሩለት።

 በወቅቱ የነበረውን እውነትም የእግዚአብሔር ቃል እንደሚከተልው ይገልጸዋል።

“---በሰንበትም መጨረሻ፤ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። 
 
እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። 
 
መልኩም እንደ መብረቅ፤ ልብሱም እንደ በረዶ፤ ነጭ ነበረ። 

ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ፤ እንደ ሞቱም ሆኑ። 
 
መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤ 
እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና! በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። 

ፈጥናችሁም ሂዱና  ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ፤ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው። እነሆም፥ ነገርኋችሁ፤ አላቸው።

ሴቶቹም በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ። 
 
እነሆም፥ ኢየሱስ  አገኛቸውና ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። 
በዚያን ጊዜ ኢየሱስ አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው። ---” ማቴ.28፡1-10

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድል አድራጊነት ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ፤ ወይም ከተነሣባት ቅጽበት ጀምሮ እስከ እርገቱ ድረስ ለወንዶችና ለሴቶች፤ በአንድነትና በየግል፤ በቀንና በሌሊት፤ በዝግ ቤት፤ በመንገድም እየተገለጸ የተቸነከሩትን እጆቹንና እግሮቹን፤ በጦር የተወጋውን ጎኑን፤ በማሳየትና፤ ከሞት የተነሣው እርሱ ራሱ መሆኑን፤ የማይጨበጥ የማይዳሰስ፤ የማይታይም መንፈስ እንዳልሆነ፤ ለማረጋገጥ ተናገረ፤ ተራመደ፤ ተዳሰሰ፤ በላም።

ከትንሣኤው በኋላ እየተዘዋወረ ራሱን ለሁሉም ግልጽ ያደረገበት ምክንያትም
ኢፍትሃዊ በሆነው ሞቱ የተከዙትን በተለይ ተከታዮቹን ለማጽናናት፤
ትንሣኤው እውነት መሆኑን ቃል በቃል ለማረጋገጥ፤ እንዲሁም የመጨረሻ መመሪያዎችን ለደቀ መዛሙርቱ ለማስተላለፍና ለመሳሰሉት ነው

“--ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው---”። የሐዋርያት ሥራ 1÷3

ከትንሣኤው በኋላ ለሚከተሉት ሰዎች እንደሚከተለው ተገለጠ

1.      በመጀመሪያ ለመግደላዊት ማርያም፤ ዮሐንስ 20፡ 11-18

2.     ለመግደላዊት ማርያምና ለያእቆብናት ማርያም ማቴ.28፡9

3.      ለቅዱስ ጴጥሮስ ሉቃስ 24፡34፤ 1ኛ ቆሮ 15፡5

4.     በኤማሁስ መንገድ ለሁለቱ መንገደኞች(ሉቃስና ኒቆዲሞ) ሉቃስ 24፡13

5.      ከቶማስ በስተቀር ለቀሪዎቹ ሐዋርያት (ለ10) ሉቃስ 24፡36፤ ዮሐንስ 20፡19-25

6.     በ8ኛው ቀን (በዳግም ትንሣኤ) ቶማስን ጨምሮ ለሐዋርያት ሁሉ(ለ11ዱ) ዮሐንስ 20፡26-29

7.      ለ7ቱ ሐዋርያት በገሊላ ባሕር  ዮሐንስ 21፡1-3 ((ስምኦን፤ቶማስ፤ናትናኤል፤ የዘብዲዮስ ልጆች፤ ሉቃስ፤ እና ኒቆዲሞስ  ወይም በኒቆዲሞስና በሉቃስ ፈንታ ይሁዳና ያዕቆብ)

8.      ለ500 ሰዎች ማቴ. 28፡16-20፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡6

9.     “የጌታ ወንድም” ለሚባለው ለያዕቆብ 1ኛ ቆሮ. 15፡9

10.     በዕለተ ሐሙስ ባረገባት ቀን ለሐዋርያት (11ዱ) ሉቃስ 24፡ 44-53

11.      ካረገ በኋላ ለቅዱስ ጳውሎስ በደማስቆ፡ የሐዋርያት ሥራ 9÷1-9፤ 1ኛ ቆሮ. 15፡8

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ወደ ዓለም ሂደው የምሥራቹን እንዲናገሩና ሁልጊዜም ከእነርሱ እንደ ማይለይ ቃል በመግባት የመጨረሻ  ትዕዛዛትንም ለደቀመዛሙርቱ እንደ ሚከተለው አስተላለፈ ።

“--እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ--” ማቴዎስ 28÷20
ትንሣኤ በሰዎች ሕይወት

ይህ የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጆች ከሙታን ተነስተው ለዘላለም ለመኖራቸው ማረጋገጫና መተማመኛ እንደ ሆነ በመግቢያችን አይተናል ። መጻሕፍትም እንደሚከተለው ይናገራሉ።

“--አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።  ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና።  ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና--”። 1ኛ ቆሮ. 15 20-22

በመሆኑም ሰው እንዴት ነው የሚነሣው የሚለውን ደግሞ ባጭሩ እናያለን።

በሕይወተ ሥጋ ከክፉ ሥራ ተለይቶ በፍፁም እምነት በክርስቶስ መኖር አዲስ ሕይወት በመሆኑ የእውነተኛ ክርስቲያን የመጀመሪያ ትንሣኤው ዓለምን ባዳነው በመድኃኔዓለም በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ እንደፈቃዱ መኖር ነው። ሁለተኛው ትንሣኤው ደግሞ ከሞተ ሥጋ በኋላ የሚኖረው ትንሣኤ ወይም መነሣት ነው።

ከሞተ ሥጋ በኋላ ሁሉም የሰው ዘር እንደገና የመነሣት ዕድል ቢያገኝም አነሣሱ ግን በምድራዊ ሕይወቱ የተመሠረተ ነው። ይህም ማለት “የክብርና የውርደት” የሚባሉ ሁለት የትንሣኤ ዓይነቶች አሉ።
ምድራዊ ሕይወቱን በጽድቅ ያሳለፈ የክብር ትንሣኤን፤ በኃጢአት ያሳለፈ ደግሞ “የውርደት” ትንሣኤን ይነሣል።

“በምድር ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉት ብዙዎች ይነቃሉ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፤ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና (ሐፍረት) ወደ ዘላለም ጕስቍልና” ዳንኤል 12÷23

“በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፤ ክፉም ያደረጉ ልፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ በዚህ አታድንቁ” ዮሐንስ 5÷28-30 

እንደ ልኡል እግዚአብሔር ቃልና በዘወትር ኑሯችን በግልጽ እንደምናውቀው ሰው የሆነ ሁሉ ሞተ ሥጋን የማይቀምስ የለም። ወይም በሞተ ሥጋ አማካኝነት ከዚች ከምናያት ዓለም ቀኑን ጠብቆ ይለያል።

ሞተ ሥጋ የሁሉም ሰው የጋራ ድርሻ ወይም ዕድል ፈንታ ነው፤ ሞተ ሥጋ ለሰብአዊ ፍጡር የምድራዊ ሕይወቱ ፍጻሜ ወይም መጨረሻ ነው።

“ በውኑ የሰውን ልጅ ሁሉ ለከንቱ ፈጠርኸውን? ሕያው ሆኖ የሚኖር፤ ሞትንስ የማያይ ማነው?” መዝሙር 88÷48

ስለዚህ በሞተ ሥጋ ምክንያት ሥጋና ነፍስ ተለያይተው ሥጋ ወደ ተገኘባት መሬት (ወደ አፈር)፤ ነፍስ ደግሞ ወደ አስገኛት ወደ እግዚአብሔር ከሄዱ በኋላ፤ እንደገና ቀደመው እንደ ነበሩ ሆነው ተዋሕደው በአንድ አካል ፍጹም ሰው ሆነው ይነሳሉ። ይህ የሙታን ትንሣኤ፤ እንደ ገና ሕይወት ዘርቶ የመገኘቱ ወይም የመነሣቱ ሁኔታ ትንሣኤ ይባላል።

--“አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ።--” መክብብ 12÷7

ሆኖም ግን ሥጋዊ ሞት የምድራዊ ሕይወት ፍጻሜ እንጂ የዘላለም ሕይወት ፍጻሜ ባለመሆኑ ልንፈራው እንደማይገባ ተጽፏል። መፈራት የሚገባው አንገብጋቢው ነገር ግን የክፉ ተግባር ወይም የኃጢአት ውጤት ብቻ ነው።

 ሞተ ሥጋ ግን ብንፈራውም ባንፈራውም  የማይቀር፤ ዕድል ፈንታችን ስለሆነ በመፍራት የምንፈጥረው ለውጥ የለም። ሰማያዊውን ወይም ዘላለማዊውን ቤታችንን ለመሥራት ማለትም የበለጠ ወደ አምላካችን ለመቅረብ የንስሐ ጊዜን እንድናገኝ አምላካችንን መለመን እንችላለን፤ ከዚህ ያለፈ ግን ለዘላለም በዚህ ዓለም ለመኖር የምንለምነው ልመና አይኖርም። ስለዚህ መፍራት ክፉ ተግባርን ነው፡ ክፉ ተግባር ራሱ ኃጢአት ሲሆን የኃጢአት ደመወዝ ደግሞ ሰማያዊ ወይም ዘላለማዊ ሞት ነው። ለዘላለም ከአምላክ መንግሥት መለየት ነው። ይህ ነው ሊፈራ የሚገባው።

በመሆኑም ትኩረታችን ከሞተ ሥጋ በኋላ ባለው ሁኔታ ሊሆን ይገባል።
ይህም ክርስቶስ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕይወቱን ሰጥቶ መሥዋዕት ሆኖ አድኖን፤ ሙሉ የልጅነትና የወራሽነት ሥልጣንን ሰጥቶናል፤ ከዚህ በኋላ ክብራችንን ጠብቀን፤ አባትነቱን፤ መሥዋ ዕትነቱን እና ልጅነታንንም አክብረን እንደ እርሱ ፈቃድ ከኖርን የክብርን ትንሣኤ ተነሥተን የዘላለምን የአባታችንን መንግሥት እንወርሳለን፡፡

አንድ ልናውቀው የሚገባ ነጥብ ግን ይህ የተሰጠው የዘላለም ድኅነት እንዲሁ በሰብአዊነታችን ወይም ክርስቲያን ተብለን በመጠራታችን በውርስነት የሚተላለፍ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ሕይወትንና ክርስቲያናዊ ሥነምግባርን የሚጠይቅ ነው። ለዚህም ነው። ትንሣኤ ዘለክብር እና ትንሣኤ ዘለሐሳር የሚጠብቀን። የክብርና የውርደት ትንሣኤ ማለት ነው። መንግሥተ ሰማያትና ገሐነመ እሳት ማለት ነው። ስለዚህ የግላችን ምርጫ ነው። የትኛውን ትንሣኤ መነሣት እንደምንፈልግ መምረጥ ብቻ ነው።

ምን አልባት ዲያብሎስ ታሠረ አዳም ነጻ ወጣ እያልን ተዝናንተን ክርስቲያናዊ ሕይወታንን ረስተን ፤ በስም ክርስቲያንነት እየተመካን እንዳንታለል። ዲያብሎስ ከመብት ጥያቄው ተሻረ እንጂ በእሥር ቤት እንዳለ ወንጀለኛ እጁቹን እና እግሮቹን ታሥሮ መንቀሳቀስ የማይችል ሽባ እንዳይመሥለን። የምርጫ ጉዳይ ነው። እኛ መርጠን ለርሱ የተጋለጥን ሆነን በፈቃዳችን ከተከተልነው የመቀበል መብትና እንደገና የመማረክ ኋይል አለው።

 ለዚህም ነው ይህ የሚሰበከው ሰላምና ደስታ ለሁላችን ወይም ለዓለም ሁሉ በባለቤት ከተሰጠ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ አልፏል። ዓለም ግን አሁንም ከደስታና ከሰላም ፍጹም የተራቆተ ነው። ለምን? ዲያብሎስ አሁንም እርሱን የሚከተሉትን ይዙ የመሞት ኃይል ስላለው።

ከአምላክ ዘንድም መብት ተሰጥቶታል፡ “--የመጻሕፍቶቼን ቃልና ትዕዛዜን ትተው ወደ አንተ ከመጡ እኔንም ጥፋታቸው አያሳዝነኝም--” 3ኛ መቃብያን 12÷3 ይህ ከእግዚአብሔር  ለዲያብሎስ የተሰጠ መልስ እንደሆነ ተገልጾ መጽሐፈ መቃብያን በሚባለው መጽሐፍ የሚገኝ ነው።

ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ “--በመጠን፤ ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት-”። 1ኛ ጴጥሮስ 5÷8-9

 እኛ ግን የመቃወም እና አንፈልግህም የማላት ሙሉ ነጻነትና ኃይል አለን። ስለዚህ ዲያብሎ ታሠረ ማለት እኛ በፈቃዳችን ካልተከተልነው በስተቀር እርሱ “አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ”(አዳም የዲያብሎስ አገልጋይ፤ ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ) ተብለን እንደነበረው እንደ ጥንቱ አሁን በዚያ ዓይነት መልኩ በእኛ ሕይወት ሕጋዊ ሥልጣን የለውም። ያ የዲያብሎስ ሥልጣን እና የሰው ልጆች ለእርሱ ተገኝነት በመድኃኔ ዓለም ሞትና ትንሣኤ ተሽሯል። ማለት ነው።

ከአሁን በኋላ በዓለም መድኃኒት በመድኃኔ ዓለም በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምንና  እንደ እርሱ ፈቃድ በእርሱ ሥር የሚኖርም ሁሉ አይሞትም፤ ቢሞት እንኳን ይነሣል፤ ለዘላለምም በሕይወት እንደገና ይኖራል። ምክንያቱም እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ነውና ።

“---ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤  ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤---” ዮሐንስ 11÷25-26  ትንሣኤና ሕይወት የሆነው ጌታ አምላክ መድኃኔዓለም ለሕይወት ለክብር ትንሣኤ ያብቃን።

“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በአቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሠሮ ለሰይጣን፤ አግአዞ ለአዳም፤ እምይእዜሰ ኮነ ፍስሐ ወሰላም።


ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን


No comments:

Post a Comment