Blog Archive

Sunday, January 18, 2015

ጥምቀት/Timket/Epiphany

ጥምቀት/Timket/Epiphany

ጥምቀት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. 3፡3

እንኳን ለጥምቀት በአል በሰላም አደረሳችሁ፤ በባሕርዩ ቸርና ሁሉን ቻይ የሆነ አምላቻችን አሁንም የንስሃ ጊዜን ጨምሮልን ለሚቀጥለው ዓመት በሰላም አድርሶን ይህንን በአል ለማክበርና ድንቅ ሥራውን ለመመስከር ያብቃን።
በዛሬው ትምህርታችን ስለ  ጥምቀት ምንነት፤ ታሪክና መልእክት አጭር ትንታኔ እሰጣለሁ እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋሉን ያድለን።

ጥምቀት፡

የጥምቀት ትርጉም፦ 

ጥምቀት ማለት ቀጥታ በቋንቋነቱ ሲተረጎም በተከማቸ ውሃ ውስጥ መነከር ማለት ሲሆን ይዘቱን በተመለከተ በእምነታችን ሲገለጥ ግን በተጸለየበት ውሃ ውስጥ በሥላሴ ስም ተጠማቂውን ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አድርጎ የማውጣቱ ሂደት ጥምቀት ይባላል።

ሁላችሁም እንደምታውቁት በየአመቱ የጥምቀትን በአል ከጥር 10 ቀን ጀምረን እናከብራለን።  ታቦታት ከየመንበረ ክብራቸው ጥር አሥር ቀን ወጥተው  ወይም ተነሥተው ወደ ወንዝ ወይም ውሃ ወዳለበት ቦታ በመሄድ በውኃ ዳር ለ11 አጥቢያ ያድራሉ (በአሥራ አንድ የጥምቀት ዕለት ማታ አካባቢ ይመለሳሉ። የሚካኤል ታወት ካለ በማግሥቱ  የሚካኤል በአል ስለሆነ ለሁለተኛ ቀን አድሮ በ12 ወደ ቤተ መቅደሱ ይመለሳል።) ውሀ በሌለበት አካባቢም በልዩ ልዩ መሣሪያዎች ወይም ዕቃወት ውኃው እንዲከማች ይደረጋል። 

የተከማቸውም ውኃ  ከተጸለየበት በኋላ ለምእመናን ይዳረሳል። ቦታው የዮርዳኖስ ወንዝን፤ ውኃው የዮርዳኖስ ውሀን የሚተካ ነው።

የታቦታት ወደ ወንዝ መውረድና የውሐው ምሳሌ

1.      ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ወጥተው በወንዞች ወይም ውሀ ባለበት አካባቢ የሚያድሩት ምክንያትም ታቦት የጌታ ማደሪያ ስለሆነ  ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በትኅትና የመሄዱን ምሳሌ ለማሳየት፤ ትኅትናውን ለማሰብና ለመግለጽ ነው።

2.     ውኃው በጸሎት ተባርኮ ለምእመናን የሚረጭበትም ምክንያት ጌታችን የባረከውን ውኃ በመከፋፈል የእርሱን በረከት ለማግኘት ነው። በዚህ ጌዜ የሚጸለየው ጸሎት ሁሉ በዚያን ጊዜ በዮርዳኖስ የተፈጸሙ ታሪኮችና በነቢያት ስለጥምቀትና ስለዮርዳኖስ ወንዝ ወይም ውሃ የተነገሩ ወይም የተተነበዩ ትንቢቶች ናቸው።

ጥምቀት
·         ከመገለጥ በአላት አንዱ ነው ማለትም አምላክ ራሱን ለዓለም ከገለጠባቸው መንገዶች አንዱ የጥምቀት በአል ነው።
·         ለሰው ልጆች ወደ ክርስትና ሕይወት ለመግባት የመጀመሪያው በር ነው
·         በአዳምና በሔዋን ምክንያት ያጣነውን የእግዚአብሔርን ልጅነት መልሰን የምናገኝበት መንገድ ነው
·         በአዳም ምክንያት ከተላለፈብን ኃጢአትና ከጊዜ በኋላ ራሳችን ከምንሠራው ኃጢአት የምንነጻበት ነው
·         ያልተጠመቀ ሰው የመዳን ዕድል የለውም “”

·         ሰው ሲጠመቅ ሁለተኛ ተወለደ ይባላል።
ጥምቀት ሁለተኛ ልደት የተባለበትም ምክንያት አንደኛ ልደት ከአባትና ከእናት በሥጋ መወለድ ሲሆን ሁለተኛው በማይመረመር የአምላክ ጥበብ በውሃ ተጠምቀን በመንፈስ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ስለምንወለድ ነው።
እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልምዮሐ. 3፡3

ጥምቀት በስንት ይከፈላል?፡

ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀት፡-

ጥምቀት አንዲት ናት፤ ሆኖም ግን የንስሐ ጥምቀት የሚባልም ስላለ የልጅነት እና የንስሐ በመባል በሁለት ይከፈላል። መጽሐፍ ቅዱስና የሃይማኖት ጸሎት “በአንዲት ጥምቀት እናምናለን” ሲሉ የልጅነት ጥምቀትን መጥቀሳቸው ነው። ብዙ ጊዜ ቅዱሳት መጻሕፍት ልጅነትን ስለምታሰጥ ጥምቀት ስለሆነ የሚናገሩት ጥምቀት አንዲት ናት ይላሉ። “..አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት…” ኤፌ.4፡5

የንስሐ ጥምቀት፦ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ጥምቀቶች የሚል ብዛትን ወይም ከአንድ በላይ መሆናቸውን  ጽፏል። ምክንያቱም የንስሐን ጥምቀት በመጨመር በብዙ ቁጥር መናገሩ ነው። “…እርሱም  ከሞተ ሥራ ንስሐና በእግዚአብሔር እምነት፥ ስለ ጥምቀቶችና እጆችንም ስለ መጫን ስለ ሙታንም ትንሣኤ ስለ ዘላለም ፍርድም ትምህርት ነው…” ዕብ 6፡ 2

ስለ ንስሐ ጥምቀት ዋና ምሳሌ ከሚሆኑን ጥቅሶች መካከል መጥምቁ ዮሐንስ ሲያጠምቀው የነበረው ጥምቀት አንዱ ነው። እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤ ማቴ.3፡11

እንዲሁም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስም በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደ ሚከተለው ጳውሎስ የተናገረውን ጠቅሶ ጽፏል። “…እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም ። በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። ጳውሎስም። ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው…”። የሐዋርያት ሥራ፡ 19፡3


የጥምቀት ምድብ ወይም አመዳደብ፡-

ጥምቀት ከ5ቱ አእማደ ምሥጢር አንዱ ምሥጢር ሲሆን በ3ኛ ተራ ቁጥር ይገኛል። አምስቱ አእማደ ምሥጢር የሚባሉት
1.      ምሥጢረ ሥላሴ (የሥላሴ ወይም የሦስትነት ምሥጢር)
2.     ምሥጢረ ሥጋዌ(ሰው የመሆን ወይም የተዋሕዶ ምሥጢር)
3.     ምሥጢረ ጥምቀት(የጥምቀት ወይም የመጠመቅ ምሥጢር)
4.     ምሥጢረ ቁርባን እና(የቁርባን ወይም የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምሥጢር)
5.     ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ናቸው።(የትንሣኤ ሙታን ወይም ከሞተ ሥጋ በኋላ የመነሣት ምሥጢር)

ከ7ቱ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትም ደግሞ አንዱ ጥምቀት ሲሆን በ1ኛ ተራ ቁጥር ይገኛል።
7ቱ የቤ/ክ ምሥጢራት የሚባሉት ደግሞ
1.      ምሥጢረ ጥምቀት (የጥምቀት ምሥጢር)
2.     ምሥጢረ ሜሮን(የሜሮን ወይም የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሚተላለፍበት ቅባት ምሥጢር)
3.     ምሥጢረ ንስሐ( የንስሐ ወይም በሠሩት ኃጢአት ተጸጽቶ በመመለስ ከኃጢአት የመንጻት ምሥጢር)
6.     ምሥጢረ ቁርባን (የቁርባን ወይም የቅዱስ ሥጋውና የክቡር ደሙ ምሥጢር)
4.     ምሥጢረ ክህነት( የሥልጣነ ክህነት ምሥጢር)
5.     ምሥጢረ ተክሊል (የተክሊል ወይም ሁለት ተቃራኒ ጾታዎች  በጸሎት አንድ የሚሆኑበት ምሥጢር) እና
6.     ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው። (የቀንዲል ወይም ሰዎች ከልዩ ልዩ ህመም የሚድኑበት ቅባት ምሥጢር)
እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሁሉ ምሥጢር የተባሉበት ምክንያት ምስጢር ማለት ስውር በአይን ሊታይ በእጅ ሊዳሰስ የማይችል ረቂቅ ማለት ሲሆን በነዚህ ምሥጢራት ወይም የጸሎት ክፍሎች አማካኝነት በሚታዩ ካህናት ጸሎት እና በሚታዩ ንዋያተ ቅድሳት የማይታይ የእግዚአብሔር ጸጋ ስለሚገኝባቸው ነው።

ክርስቶስ ለምን ተጠመቀ?

1ኛ አምላክነቱን ለማሳየት ወይም ለመግለጥ ሲሆን አገላለጹም እንደ ሚከተለው ይሆናል።
·         እግዚአብሔር ወልድ ድምጹን በማሰማት አሰማ እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለማቴ.3፡17

·         እግዚአብሔር ወልድ በአካል በዮሐንስ እጅ እየተጠመቀ በመታየት ተገለጸ “...ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ.. ማቴ.3 13፣16

·         እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በእግዚአብሔር ወልድ ላይ አረፈ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየማቴ. 3፡16

በመሆኑም ከዚህ በላይ በተፈጸሙት ተአምራት የእግዚአብሔር ሦስትነት ወይም የሥላሴ ምስጢር ተገለጠ የክርስቶስ በተዋሕዱ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ መሆን ተረጋገጠ፤ ማለት ነው።

2ኛ እሱ ተጠምቆ ምሳሌውን ወይም አርአያውን ለእኛ ለመስጠት እና
3ኛ ጥምቀትን ባርኮ ለእኛ ጥምቀት ኃይልን ለመስጠት የሚሉት ናቸው።

ጥምቀት ይደገማል ወይስ ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው? ልጅነትን የምንቀበልባት ጥምቀት አንድ ብቻ ናት። አትደገምም ነገር ግን የንስሐ ጥምቀት የሚባለው ብቻ ሊደጋገም የሚችል ነው።

አጥማቂው ማነው?

ጥምቀት በሁለቱ የክህነት ደረጃዎች ብቻ ይፈጸማል በኤጲስ ቆጶስና ( ኤጲስቆጶስ የሚባለው ጳጳስ ነው) በቄስ ብቻ፤ ዲያቆናትና ምእመናን እንዲሁም ሥልጣነ ክህነት የሌላቸው መነኮሳት  ግን ማጥመቅ አይችሉም። ምክንያቱም ክርስቶስ እንዲያጠምቁ ያዘዛቸው ሐዋርያትን ነው፤ ሐዋርያትም የኤጲስቆጶስነት ወይም የቅስና ሥልጣን ነው የነበራቸው።

ተጠማቂዎቹ እነማን ናቸው?

ማነኛውም በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ወንድ፤ሴት፤ ሕጻን፤ ሽማግሌ፤ ነጭ፤ ጥቁር፤ በአጠቃላይ ለሰው ዘር ሁሉ የተፈቀደ ሲሆን መመዘኛው ማመን ብቻ ነው። “…በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው።  ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ።  ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም…” የሐዋርያት ሥራ 8፡ 36-38። 

የጥምቀት ዕድሜ፡

ለመጠመቀ  የዕድሜ ክልልህ አልፏል ወይም አልደረሰም ስለዚህ መጠመቅ አትችልም የሚል ሕግ የለም። በማነኛውም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሁሉ መጠመቅ ይችላል። የክርስቲያን ልጆች ከሆኑና የመጠመቅ ዕድል ካገኙ ወንድ በተወለደ በ40 ቀኑ ሴት በተወለደች በ80 ቀኗ በክርስትና አባት ወይም እናት ኃላፊነት በተወካዮቻቸው በኩል እምነታቸውን እየመሠከሩ መጠመቅ አለባቸው።

ለምን በ40 እና በሰማንያ ቀናት እንጠመቃለን (የክርስቲያን ልጆች)?

ባጭሩ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ሲሆን መሠረቱን እንደሚከተለው እንመልከት።
1ኛ በዘመነ ብሉይ እሥራኤላውያን ወንድ ከወለዱ በ40 ቀኑ፤ ሴት ከወለዱ በ80 ቀኗ ወደ ቤተ መቅደስ ወስደው በስማቸው መሥዋዕት ያቀርቡላቸዋል፤ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሟቸዋል በመሆኑም ከዚያች ዕለት ጀምረው ከእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ይቆጠራሉ ማለት ነው። ዘጸ. 12፡1፤ ዘጸ. 4፡22፡፤ ይህ ሥርዓት ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስም ተከናውኖለታል። ሉቃስ፡2፡22

2ኛ በመጽሐፈ ኩፋሌ ተጽፎ እንደሚገኘው፡ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ፤ ሔዋን በተፈጠረች በ80 ቀኗ አምላካቸው እግዚአብሔር በጸጋው ከወለዳቸው በኋላ ብርሃንን አልብሶ ብርሃንን አጎናጽፎ ወደ ገነት አስገብቷቸዋል። “… ለአዳም 40 ቀን ከተፈጸመለት በኋላ ወደ ገነት አስገባነው፤ ሚስቱንም በ80 ቀን አስገባናት…” ኩፋሌ 4፡9። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቲያን ልጆች በክርስትና አባትና እናት ሐላፊነት በ40 እና በ80 ቀናት እንዲጠመቁ ታዛለች።
መጽሐፍ ቅዱስ በማርቆስ ወንጌል 16፡ 15-16 ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ። 

ያመነ የተጠመቀም ይድናል፥ ያላመነ ግን ይፈረድበታል ስለሚል ሰው መጠመቅ ያለበት ተምሮ፤ አምኖ እራሱ እምነቱን እየመሠከረ መሆን አለበት በማለት የ40 እና የ80 ቀን ጥምቀትን የሚቃወሙ አሉ። ሆኖም ግን “ አምኖ እምነቱን እየመሠከረ መጠመቅ አለበት” የሚለውን ቤተ ክርስቲያናችን በሚገባ ትቀበለዋለች፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው። በ40 እና በ80 ቀናት መጠመቅ አይገባም የሚለውን ግን ቤተክርስቲያን አትቀበለውም።

 ምክንያቱም  መጽሐፍ ቅዱስ በ40 እና በ80 ቀናት መጠመቅ አይገባም አላለም፤  ስለ እምነታቸው ተምረው፤ እምነታቸውን እየመሠከሩ መጠመቅ ያለባቸው 1ኛ በልዩ ልዩ ምክንያት በ40 በ80 ቀናት ወይም ከዚያም በኋላ የመጠመቅ ዕድል ሳያገኙ የቆዩ ከሆኑ፤ 2ኛ ከእስልምናና ከሌሎች የእምነት ድርጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኦርቶዶክስ እምነት ለመመለስ ወስነው የሚመጡ ሲሆኑ እነዚህ ሰዎች አስተማሪ ተመድቦላቸው ተምረው አውቀው እምነታቸውን እራሳቸው እየመሰከሩ ይጠመቃሉ። የክርስቲያን ልጁች ግን እምነታቸውን ራሳቸው የመመስከር ችሎታ እስከሚኖራቸው የእድሜ ክልል ድረስ መጠበቅ የለባቸውም።

ይህም የሆነበት ምክንያት፡

1ኛ፡ ከላይ በዘጸአትና በመጽሐፈ ኩፋሌ እንዳየነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌነት አለው። መጽሐፍ ቅዱስም የ40 እና የ80 ቀናት ጥምቀትን አልከለከለም።

2ኛውና ዋናው ግን  እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ዮሐ. 3፡3 ስለሚል ሁለተኛ መወለድ ማለት ድግሞ መጥመቅ ማለት ነው። ስለዚህ ዕድሜያችን ለትምህርት ደርሶ እምነታችን እየመሠከርን ለመጠመቅ ከመቻላችን በፊት በሞተ ሥጋ ብንለይ ከመንግሥቱ ተለይተን እንዳንቀር በማሰብ በ40 እና በ80 ቀናት እንጠመቃለን።

አሁንም ሕጻናት ለሞት ሊያደርስ በሚችል ሕመም መያዛቸው ከታወቀ በማነኛውም የዕድሜ ገደብ ማለትም ከ40 ከ80 ቀናትም በፊት መጠመቅ እንደሚችሉ ቤተ ክርስቲያን ታዛለች። ፍትኃ ነገሥት አንቀጽ 3
በማን ስም እንጠመቃለን?

“እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. 28፡ 20 ላይ ቅዱሳን ሐዋርያትን ባዘዛቸው መሠረት በሥላሴ ስም እንጠመቃለል።

ክርስቶስ የተጠመቀው በ30 ዓመቱ ስለሆነ ለምን እኛ በ30 አመታችን አንጠመቅም ?

ስለሰዎች የጥምቀት ዕድሜ  መጀመሪያ ላይ “የጥምቀት ዕድሜ” በሚለው ርእስ አይተናል ። የክርስቶስ በ30 ዓመት መጠመቅ ግን ምሳሌነቱ ለጥምቀት ዕድሜ ሳይሆን ለክህነት አገልግሎት ነው።

ምክንያቱም ወዲያውኑ እንደተጠመቀ ወደ ጾምና ወደጸሎት በመሄድ 40 ቀንና 40 ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ የክህነት አገልግሎቱን ሐዋርያትን በመምረጥ ጀመረ። በመሆኑም በዚህ ምሳሌ መሰረት ቅስና የሚቀበል ሰው ዕድሜው ከ30 ያነሰ መሆን እንደሌለበት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተሠራ።


በጥምቀት የሚገኘው ጥቅም፡

1.      ከእግዚአብሔር መወለድ
2.     ከአዳም እና በግላችንም ከሠራነው ኃቲአት መንጻት
3.     በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ልጆች እንደ መሆናችን መጠን የአባታችንን የዘላለም መንግሥት ለመውረስ ዕድል ማግኘት
4.     አዲስ ስምን ማግኘ፤ ትክርስቶሳውያን መሆን እና በክርስቶስ “ክርስቲያን” የሚለውን የዜግነት ስም ማግኘት

·         የክርስትና አባት ወይም እናት ማግኘት ማነኛውም ተጠማቂ የክርስትና አባት ወይም እናት ያስፈልገዋል፡፡

 ለቅዱሳንና ለእግዚአብሔር እንሰጣለን የሚሉ ወላጆች መስጠት ቢችሉም አሁንም ቅዱሳንን ወይም እግዚአብሔርን ወክሎ ስለ እምነት የሚወከል ስለሚያስፈልግ በእለቱ የሥርዓተ ጥምቀቱን ጸሎት የሚያደርሱ ካህናት መወከል ይችላሉ።

ነገር ግን በፍትሐ ነገሥት መሠረት ያላገባ ዲያቆን ሴት ልጅን ክርስትና ማንሳት አይችልም። ስለዚህ ቄሱ ወይም ዲያቆናዊት ሴት መወከል ይችላሉ።


ከጥምቀት በኋላ ምን ማድረግ አለብን?

ከጥምቀት በኋላ አምላካችን በሰጠን ዕድል መሠረት በውሃና በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀን ሁለተኛ ተወልደን የእግዚአብሔር ልጆች ሆነናል፤ ስለዚህ ወደ ኋላችን ሳንመለስ በደሙ አጥቦ ቀድሶ ከኃጢአት ንጹሐን አድርጎ አዲስ ፍጥረት አድርጎ እንዳከበረን ክብራችንን ጠብቀን በክርስትና ሥነ ምግባር ጸንተን መኖር ነው። “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል”2ኛ ቆሮ. 5፡ 17

“…በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት።  የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም…” ኤፌ.4፡27-28።

እንደ ሰውነታችን ነገሮች ከጠበቅናቸውና ከአቅማችን በላይ ሆነውብን በኃጢአት ስንወድቅም በልባዊ ንስሐ እየተመለስን የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ማፍራት መቻል አለብን። ስምን ብቻ ተሸክመን  ታሪክን እየተረክን፤ በታሪክና በባለታሪክ እየተመካን ለውጥ በሌለው ንስሐ፤ ፍሬ በሌለው ክርስትና ተደብቀን የምንኖር ከሆነ ግን የስም ክርስቶሳዊነት የአምላክን መንግሥት ሊያወርሰን አይችልም።
“ እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤  በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።  አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል”። ማቴ. 3፡8-10

 ማለትም እግዚአብሔር መንግሥቱን ሊያወርሰን ወይም ለአብርሃም ያደረገውን ሁሉ ሊያደርግልን የሚችለው የአብርሃምን ታሪክ በመተረካችን ሳይሆን የአብርሃምን ሥራ በመሥራታችን ብቻ ነው ማለት ነው።

ልዑል እግዚአብሔር ሰምተን ለመማር ወይም ለማወቅ አውቀን ለመሥራት ሠርተንም ለመዳን እንድንችል በቸርነቱ ይርዳን ።
for video click this link


3 comments:

  1. ጸበል በካህን መረጨት ከጥምቀት ጋር ይመሳሰላል? ሴቶች ከወለዱ በኋላ ቤቱ እንዲረጭ የሚደረገው ለምንድን ነው?

    ReplyDelete
  2. አራስ ቤት ገብቶስ ጸበል ሳየረጩ ቤተ ክርስትያን መግባት ይቻላል?

    ReplyDelete
  3. Respect and that i have a super provide: How Much Is House Renovation Loan In Pag Ibig house renovation exterior

    ReplyDelete