Blog Archive

Do you know this part 1,2, and 3

Do You Know This? part 1


ይህንን ያውቃሉ? የተሰኘው ይህ ተከታታይ ትምህርት በእምነትና በማኅበራዊ ሕይወትም ጭምር በብዙኃኑ ዘንድ ጎልተው የማይታወቁ ቃላትን ሕግጋትን፤ሥርዓታትን፤ እና አባባሎችን የምንተረጉምበትና የምናውቅበት መድረክ ነው።

ይህንን ያውቃሉ? /Do you know this?

ይፍቱኝ የምንለው መቼ ነው?


እግዚአብሔር ሁሉንም የሚያውቅ፤ ሳንጠይቀው የምንፈልገውን አውቆ የሚሰጠን፤ ለጋስ፤ ሁሉን ቻይና መኃሪ አምላክ ቢሆንም፤ በተቻለ መጠን በሥርዓቱና ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ሐሣባችን ማቅረቡ ለኅሊናችን ርካታን ይሰጠዋል፤ ሌሎችንም ለማስተማር ብቁዎች እንሆናለን ምክንያቱም ትምህርታችን ስሜትን የሚሰጥ ትንታኔ  ስለሚኖረው ነው።
ካህኑ “እግዚአብሔር ይፍታ” ከማለቱ በፊት ይፍቱኝ እንበል። ይህንን በማለት ጥያቄ ወይም ልመና ማቅረባችን ነው።

ካህኑ “እግዚአብሔር ይፍታ” ሲል ደግሞ አሜን እንበል ። አሜን ማለት ይሁን ይደረግ ማለት ስለሆነ ካህኑ ጥያቂያችንን ተቀብሎ 
“እግዚአብሔር ይፍታ” በማለቱ ያልከው ቃል ይደረግልኝ በማለት ምኞታችንን ማቅረባችን ነው። to watch video click here:ይፍቱኝ


Do You Know This? part 2

ኪሪዬ ኤሌይሶን





v  እግዚኦ ተሰሀለነ
v  አቤቱ ይቅር በለን
v  ኪሪዬ ኤሌይሶን
በቅዳሴ ጊዜ ዲያቆኑ በ እንተ ቅድሳትን ሲል በሌሎችም የጸሎት ክፍሎች ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ሦስት ቃላት በማከታተል ስንናገራቸው ወይም ስንጸልያቸው እንሰማለን ሆኖም ግን 
ሦስቱም አንድ አይነት ትርጉምን ይሰጣሉ  ወይም አላቸው
·        እግዚእ = ጌታ
·        ኪሪዬ= ጌታ (ጌታዬ)
·        ኤሌይሶን=ይቅር በለን
·        አቤቱ(ጌታሆይ) ይቅር በለን
·        ተሰሀለነ=ይቅር በለን

በመሆኑም በሦስት ቋንቋ መናገር አይኖርብንም። ትርጉም የሚያስፈልጋቸውን እየተረጎመ፤ እያብራራ፣ በተለያዩ ምሳሌዎች እየቀመመ ከወቅቱና ከ እኛም ሕይወት ጋር እያገናዘበ ማስተማር ያለበት ሰባኬ ወንጌሉ ነው፤ የትምህርትና የማብራርያ የመተርጎሚያም ጊዜ ከቅዳሴው በኗላ ነው። ቅዳሴው ግን ጽሎት ስለሆነ የተጻፈውን ሳንቀንስ፤ ሳንጨምር በስርዓቱ መሠረት ልመናችንን ሁሉንም ለሚሰማ ልቡናን ለሚመረምር ልዑል አምላክ የምናቀርብበት ጊዜ ነው። ስለዚህ በአንዱ ቋንቋ ብቻ (ቅዳሴው በግእዝ ከሆነ “እግዚኦ ተሰሐለነ” በአማርኛ ከሆነ “አቤቱ ይቅር በለን” በግሪከኛ ከሆነም “ኪሬ ኤሌይሶን”) በማለት እንጸልይ።
 to watch video click here፡ ኪሬዬ ኤለይ ሶን!
part 3


ሲያሳልሙና ሲሳለሙ




ካህኑ እያንዳንዱን ፆታ ምእመን በመስቀል ወይም በእጁ ሲባርክ ወይንም ሲያሳልም ምን እንደ ሚል ያውቃሉ?
እግዚአብሔር አምላክ በመጽሐፈ ዘሁልቍ ምዕራፍ 6 ቍጥር 22 ላይ ለነቢዩ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ካህናት በሚባሩኩ ወይንም በሚያሳልሙን ጊዜ  በሚከተለው የሕያው እግዚአብሔር ቃል በመመረቅ ወይም በመባረክ ወይንም  መልካም ምኞትን በመመኘት ነው ወይንም እግዚአብሔር ራሱ በሰጣቸው የመባረክ ስልጣን በረከትን በማደል ነው። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት  እያንዳንዱን ፆታ ምእመን የሙያውን ደረጃ፤ ወይም ዓይነትና የሕይወት ምርጫውን መሠረት በማድረግ በሚከተሉት የበረከት ዐረፍተ ነገራት ይባርኩታል።
ካህኑ፦
1.      የቅስና ማእረግ ያለውን ካህን ሲያሳልም፦ ሢመተ እዴሁ ለአቡነ ጴጥሮስ ወይም በአማርኛ (“ይህ የአባታችን የጴጥሮስ ሥልጣን (የእጁ ሹመት) ነው”) ሲል ተሳላሚው ካህን “እግዚአብሔር ይሢምከ ውስተ ዘለዓለም መንግሥቱ” ወይም በአማርኛ “እግዚአብሔር በዘላለም መንግሥቱ ይሹምህ” ይልና ይሳለማል።  መጽሐፈ ቅዳሴ ገጽ 139።
የቅስና ሥልጣን ያለውን ካህን በቅዱስ ጴጥሮስ ስም ይሚያሳልምበት ምክንያት ካህናት የዓለም ኃያላን መንግሥታት በኅብረት ሊፈቱት ወይም ሊሽሩት የማይቻላቸውን መለኮታዊ ሥልጣን ከክርስቶስ የተቀበሉት በሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በኩል ስለሆነ ነው ። ማቴዎስ ም.16 ቍ.18-20

2.     ዲያቆናትን ሲያሳልም፦ “በረከተ ጳውሎስ/እስጢፋኖስ ይህድር በላእሌከ (የጳውሎስ/እስጢፋኖስ በረከት በአንተ ላይ ይደር) በማለት ሲያሳልመው ዲያቆኑ አሜን በማለት ይሳለማል።


ዲያቆኑን እግዚአብሔር ልዑል ይባርከ ወያብርህ አዕይንተ አልባቢከ (ልዑል እግዚአብሔር ይባርክህ ዐይነ ልቡናህንም ያብራልህ) በማለትም ልባርከው ይችላል፡

ዲያቆኑን በቅዱስ ጳውሎስና በቅዱስ እስጢፋኖስ ስም መባረኩ፡ ቅዱስ ጳውሎስ ምእመናንን በመልእክቱ ያስተማረ፤ የእግዚአብሔር ፈጣን መልእክተኛ ሲሆን እስጢፋኖስም የመጀመሪያው ዲያቆን ወይም የእግዚአብሔር አገልጋይ ታዛዥ ስለነበረ  ዲያቆኑን የጳውሎስንና  የእስጢፋኖስን የአገልግሎት ፈለግ እንዲከተል መመረቁ ነው።




3.     መነኮሳትን ሲያሳልም፦ በረከተ እንጦንስ ወመቃርስ ይህድር በላእሌከ ወይም በአማርኛ (የእንጦንስና የመቃርስ በረከት በአንተ ላይ ይደር) በማለት ያሳልማቸዋል።

አባ እንጦንስና አባ መቃርስ የሚባሉት ምንኩስናን የመሠረቱ አባቶች ናቸው። ስለዚህ መነኮሳትን በቅዱስ እንጦንስና በቅዱስ መቃርስ ስም መባረኩ እነሱን ያጸና አምላክ የእነሱን ፈለግ የምትከተሉ እናንተንም እንደ እነሱ ያጽናችሁ በማለት መመረቁ ነው።

 መዘምራንን ሲያሳልም፦ በረከተ ያሬድ ይህድር በላእሌከ ወይም በአማርኛ (የያሬድ በረከት በአንተ ላይ ይደር) በማለት ይባርካቸዋል።

መዘምራን በዝማሬ ትምህርት ሙያ የተሠማሩና የዜማ ደራሲ የቅዱስ ያሬድን ፈለግ የሚከተሉ ስለሆኑ ለቅዱስ ያሬድ የዜማን ድርሰት በገፍ የሰጠ ልዑል አምላክ ለእርሱ የሰጠውን ለናንተም ይስጣችሁ ለማለት ነው።


4.     ምእመናንን ሲያሳልም፦  እግዚአብሔር ይባርከ ወያብርህ ገጾ ላእሌከ” (እግዚአብሔር ይባርክህ ፊቱንም ይግለጽልህ) ይለዋል። ዘኁልቑ 6፡22
ሴቷንም “እግዚአብሔር ይባርኪ ወያብርህ ገጾ ላእሌኪ” በአማርኛ (እግዚአብሔር ይባርክሽ ፊቱንም ይግለጽልሽ) ይላታል።

(ሁሉንም በዚህ ቃል ብቻ ቢያሳልማቸው እንደ ስህተት አይቆጠርም) ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ለነቢዩ ሙሴ የተሰጠ ትእዛዝ ስለሆነ ነው።

ተሳላሚዎች አሜን ወይም ይሁን ይደረግ እያሉ ይሳለማሉ ።














5.     ምንጭ፡ ዘኍልቍ 6፡22፤ ቅዳሴ ሐዋርያት ገጽ 139 እንዲሁም ሌሎች የሥርዓት መጻሕፍትን ይመልከቱ



No comments:

Post a Comment