የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ/የእምነት ሕግ ባጭሩ
የሃይማኖት ትምህርት /ትምህርተ ሃይማኖት ክ ፍ ል 1
መ ግ ቢ ያ
በዚህ ርእሳችን ተከታታይ ትምህርትን እንማራለን
መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ይላል ምሳሌ 1፡7 ይህም የማይታበል ሐቅ ነው። የትምህርትና የሥነ ጽሁፍ ሊቃውንት በበኩላቸው “የትምህርት መጀመሪያው ስለ ሚማሩት የትምህርት ርዕስ በሚገባ መመርመር ነው” ይላሉ ።
እኔም ከዚሁ እውነት በመነሣት የያንዳንዱን የትምህርት ርዕስ ስያሜና ትርጉም ከምንጩ በመመርመር የተቻለውን ያህል ግልጽ ለማድረግ እሞክራለሁ ።
የትምህርታችን ርዕስ “ትምህርተ ሃይማኖት” ነው፤ ትምህርተ ሃይማኖት ማለት ደግሞ የሃይማኖት ትምህርት፤ ስለ ሃይማኖት ወይም እምነት የሚመረምር፤ የሚያጠና ማለት ነው፡ “ትምህርት” መሀረ አስተማረ፤ መረመረ፤ አጠና፤ ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ስም፤ ወይም ቃል ነው፡ ትርጉሙም በቁሙ ትምህርት፤ ምርምር፤ ጥናት ወዘተ. ማለት ይሆናል ወይም ነው ፤ ይህ ቃል አማርኛ ለበስ ግእዝ ይባላል ።
“ሃይማኖት ወይም እምነት” አምነ አመነ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ዘር ወይም ስም፤ ቃል፤ ሲሆን ትርጉሙም አንድን እውነት መቀበል፤ በአንድ ክፍል ላይ ተስፋ ማድረግ ወዘተ ማለት ነው። ተቃራኒው ክህደትና ጥርጥር የመሳሰሉት ናቸው።
ስለ እምነት ወይም ሃይማኖት ምሥጢራዊ ትርጉም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደሚከተለው በግልጽ አስቀምጦታል፡ “እምነትም ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚያስረግጥ የማናየውንም ነገር የሚያስረዳ ነው” ዕብ.11፡1በዚህ ቃል መሠረት እምነት ተስፋ የምናደርገው ነገር ሁሉ እርግጠኛ ስለመሆኑ፤ የማናየውንም ነገር የሚተርክ የሚያስተምር ነው ።
በመቀጠልም ሐዋርያው “ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደተዘጋጁ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን” ዕብ.11፡3 ይላል ።
በመሆኑም እምነት ስለፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር ያለውን እውነት እንዲሁም ከእርሱ ዘንድ ያለውን ተስፋችንን የሚያስረዳ፤ የሚያረጋግጥልን እውነት፤ ሁሉንም የምናይበት የልብ መነጽር ነው። ስለዚህ መንፈሳዊውን ምሥጢር ለማወቅና የአምላክን ተስፋ ለመሳተፍ ማመን እጅግ ተፈላጊና መሠረታዊ ነገር ወይም ምሥጢር ነው
“ሄኖክ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና ያለ እምነትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ፤ እግዚአብሔር እንዳለ፤ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና”ዕብራውያን 11፡5-7።
የማይታየውንና መንፈሳዊውን ምሥጢር ተቀብሎ ለማመን ደግሞ መማርና ማወቅ ግዴታ ያስፈልጋል። “እንግዲህ ያላመኑትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” ሮሜ 10፡14-17።
በዚህ የሃይማኖት ወይም እምነት ትምህርታችን ውስጥ የሚከተሉትን ሦስት አበይት የትምህርት ዓይነቶች እናያለን ወይም እንማራለን። (በዚህ በአሁኑ ደረጃ ትምህርታችን ሃይማኖትና እምነት አንድ ዓይነት ትርጉም ይኖራቸዋል)
ሦስቱ የትምህርት ክፍሎች ወይም አርእስት
1. ነገረ መለኮት
2. የአምልኮት ሥር ዓት
3. ከእምነት የተነሣ የሰዎችን አካሄድ ወይም ሃይማኖታዊ ጉዞ የሚለት ናቸው
ለሰው በሥጋዊ ሕይወቱ ለመኖር በመጀመሪያ የሚያስፈልጉት መሠረታውያን ነገሮች አሉ እነሱም
1. ምግብ
2. ልብስ እና
3. መጠለያ ናቸው።
እነዚህን መሠረታውያን ነገሮች በመጀመሪያ ካገኘ በሕይወት የመቆየት እድል ያገኛል፤ ቀስ በቀስ እያደገ ከደረጃ ወደ ደረጃ እየወጣ ኑሮውን ያስፋፋል ። ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞችን በጊዜ ሂደት ያጠራቅማል ወይም ያካብታል።
በመንፈሳዊውም ለሰው ለሰው መሠረታዊ ሕይወቱ ሃይማኖቱ ነው ። ሰው መሠረታዊ ሕይወት የሆነውን እምነቱን ካገኘ ወይም ካወቀ በመልካም ሥነ ምግባር እያደገና እየበለጸገ ይሄዳል ። ሰው እግዚአብሔር አለ ብሎ በፍጹም ልቡ ካመነ በምድራዊ ሕይወቱ ለሚያጋጥሙት በተለይ በሥጋ አስተሳሰብ አስቸጋሪ ጥያቄዎች ሁሉ ሙሉ መልስ ይኖረዋል።
ለምሳሌ፡
· ይህ የሚታየው ዓለም ከየት መጣ?
· መልካምና ክፉ ነገር ከየት ተገኘ? ይህ መልካም “ያ” ክፉ ለምን ይባላል? ወይም ተባለ?
· ከሞት በኋላ ምን ዓይነት ሁቴታ ይከሰታል?
· እኔስ በምድራዊ ሕይወቴ ምን ማድረግ ይገባኛል?
· ኢየሱስ ክርስቶስ ማነው? ወዘተ-- የሚሉ ጥያቄዎች ከራሱ ኅሊና ከውስጡ ወይም ከልዩ ልዩ ክፍሎች ሲቀርቡለት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። በሕይወቱ ሁሉም የሚገባውን በማወቁ ይረካል። ስለዚህም በዚህ ዓለም እንደሚገባው ለመኖርም ተፈላጊውን ሁሉ ያውቃል፤ የኅሊና ነጻነትም ይኖረዋል ማለት ነው።
በትምህርተ ሐይማኖት ትምህርታችን በመጀመሪያ የምንማረው ነገረ መለኮትን የምናጠናባቸውን 5ቱን አእማደ ምሥጢር ነው ። በዚህ ርእስ ውስጥ በብዛት የምንማረው ነገረ መለኮትን ቢሆንም ሥርዓተ አምልኮትንም በከፊል እናያለን (እንማራለን) ።
አምስቱ አእማደ ምሥጢር
በዚህ ርእስ ውስጥ 5 አርእስት ተጠቃለው ስለሚገኙ 5 የሚል ቅጽል ኖሯቸዋል። “አእማድ” አምድ የሚለው የግእዝ ቃል ብዜት ነው። “አምድ” ማለት የአንድን ቤት ጣራ ወይም ሁለንተና የሚሸከም ወደ ቀኝ ወደ ግራ፤ ወደፊት ወደ ኋላ፤ እንዳይዋልል ሚዛኑን ጠብቆ ቀጥ አድርጎ የሚይዝ ቋሚ ነገር ወይም መሣሪያ ነው። ከእንጨት፤ ከብረት፤ ከድንጋይ፤ ከአፈርና ወይም ከሲሚንቶ ወዘተ ሊሠራ ይችላል።
ምስጢር፡ ድብቅ ወይም ስውር የሆነ በቶሎ ሊደረስበት የማይችል ረቂቅና ሩቅ፤ለማንም የማይነገር በሁለት በሚዋደዱ ክፍሎች ብቻ የሚኖር ድርጊት ወይም ሐሣብ ወዘተ ማለት ነው። ከዚህ በላይ እንዳየነው እነዚህ አምስት አርእስት “አእማድ” የተባሉበት ምክንያት በእምነታችን ወይም በመንፈሳዊው ሕይወታችን በእምነት ጉድለት ወይም በጥርጣሬ ወደ ቀኝ ወደ ግራ፤ ወደ ፊት ወደ ኋላ እንዳንንገዳገድ ወይም እንዳንዋልል አጽንተው የሚይዙን ስለሆነ፤
ምሥጢርም፡ የተባሉበት ምክንያት በእምነት ካልሆነ በስተቀር በሥጋዊ ጥበብና በቁሳዊ ምርምር ልንደርስባቸው የማንችል ረቂቆችና ረቂቅ ጸጋን የሚያሰጡ፤ እንደ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት እንጂ ለሰዎች አስተሳሰብ የማስለሆኑ ነው።
አምስቱ አእማደ ምሥጢር የምንላቸው በቅደም ተከተል አቀማመጣቸው እንደሚከተለው ሲሆን በሁለት ይከፈላሉ፡
· ምሥጢረ - ሥላሴ
· ምሥጢረ - ሥጋዌ
· ምሥጢረ - ጥምቀት
· ምሥጢረ - ቁርባን
· ምሥጢረ - ትንሣኤ ሙታን ሲሆኑ
የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ ስለ እግዚአብሔር ያለውን ትምህርት የምንማርባቸው ናቸው። ቀሪዎቹ ሦስቱ ደግሞ የመጀመሪያዎቹን ሁለቱን ምሥጢራት ተምረውና አውቀው ላመኑ ሰዎች ስለ እምነታቸው የሚሰጡ የ እምነት ዋጋዎች ናቸው።
ልዩ መግቢያ በእነዚህ በ5ቱ አእማድ የምንማረው ባጭሩ፦
· ስለ እግዚአብሔር ባሕርይና ሕልውና እንዲሁም ለዓለም ስላደረገው የድኅነት ሥራ፤
· ስለ ዘለ ዓለማዊውና መንፈሳዊው ልጅነት
· ስለዘለዓለማዊው የሕይወት ምግብና መጠጥ
· ከሥጋዊ ሕይወት ፍጻሜ በኋላ ስላለው ዘለዓለማዊ ሕይወት ወዘተርፈ፤ ሲሆን የአምልኮትንም ሥርዓት በመጠኑ እናያለን።
ከአምስቱ አእማደ ምሥጢር የመጀመሪያው “ምሥጢረ - ሥላሴ” ነው ። ምሥጢረ ሥላሴ ማለት የሦስትነት ምሥጢር ማለት ነው። ምሥጢር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ካለፈው ትምህርታችን ስለተረዳን ከዚህ ላይ እንደገና መጥቀሱ አስፈላጊ አይሆንም ።
ሥላሴ፦ የሚለው ቃል ሰለሰ ሦስት አደረገ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ስም ሲሆን ትርጉሙ ሦስትነት (ሦስት) ማለት ነው። ስለ እግዚአብሔር ሥላሴነት ወይም ሦስትነት በምሥጢር ወይም ቀጥታ ባልሆነ አገላለጽ ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራእየ ዮሐንስ በተለያዩ ቦታዎች የተገለጸ ቢሆንም ስላሴ የሚለው ቀጥታ ቃል በቃል የሚገኘው ከ81ዱ መጻሕፍት አንዱ በሆነው በመጽሐፈ ሰራክና በሌሎችም የሊቃውንት መጻሕፍት ነው። ሲራክ 39፡21
ምስጢረ ሥላሴ፡(ይቀጥላል)
No comments:
Post a Comment