Blog Archive

Monday, April 13, 2015

Awde Tinat: ኢምክንያታዊው ፍቅርና የድኅነታችን ታሪክ/ The Unconditional Love and The History of Our Salvation

Awde Tinat: ኢምክንያታዊው ፍቅርና የድኅነታችን ታሪክ/ The Unconditional Love and The History of Our Salvation

ኢምክንያታዊው ፍቅርና የድኅነታችን ታሪክ/ The Unconditional Love and The History of Our Salvation

ኢምክንያታዊው ፍቅርና የድኅነታችን ታሪክ/ The Unconditional Love and The History of Our Salvation


ኪሬ ኤለ ይሶን፤ ኪሬ ኤለይ ሶን፤ ኪሬ ኤለይ ሶን፤ (አቤቱ ይቅር በለን)

ኢምክንያታዊው ፍቅርና የድኅነታችን ታሪክ
“--በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለምሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋእግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና--” የዮሐንስ ወንጌል 3፡16

ይህ የያዝነው ሳምንት ኢምክንያታዊው የእግዚአብሔር ፍቅር የሚተረክበት ወቅት ነው። “ስሙነ ሕማማት” በመባል ይታወቃል። የመከራ ፤የሥቃይ፤የህመም፤ ወዘተ ሳምንታት ወይም ዕለታት ማለት ነው። 

በሌላ በኩልም የ5500 ዘመን ተስፋ እውን ሆኖ በድል የተጠቃለለበት የድኅነት፤ የሰላም የደስታ የድል የነጻነት ታሪክ የሚተረክበት ወቅት ነው። ማለትም ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ፤ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው፤ ዘመን፤ ቦታ፤ የማይወስነው፤ ዓለምን ፈጥሮ ከዓለም ውጭም ያለ፤ ሁሉን ቻይ አምላክ እግዚአብሔር በፈቃዱ ብቻ የፈጠረውን የሰውን ሥጋ ለብሶ በሰው ልጆች እጅ መከራን ሊቀበል ወዶ እንዴት የድኅነትን ሥራ እንደሠራ የምንተርከበት፤ ጊዜ ነው።
እግዚአብሔር የሚለው ቃል በቋንቋነቱ  ግእዝ ሲሆን በአማርኛ “የሐገር ወይም የዓለም ጌታ” ማለት ነው። ይህ ቃል በእብራይስጥ “ኤል” የሚባለው ቃል ነው።

ሌሎች እግዚአብሔር የሚጠራባቸው  ባሕርዩንና ሥልጣኑንም የሚገልጡ ስሞቹ
ያህዌ= የነበረ፤ ያለና የሚኖር፤
አዱናይ = ጌታ ወይም ገዥ፤
ኤልሻዳይ = ሁሉን ቻይ የሚባሉት ናቸው።

እግዚአብሔር ብለን የምንጠራው የሥነ ፍጥረትን ፈጣሪ ነው ። ይህም ሰማይንና ምድርን በውስጧ ያሉትን እና የሰው ልጅ ፈጣሪው በሰጠው ጥበብ ተመራምሮ ያልደረሰበትን ፍጥረት ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ/ ባጭሩ ሁሉን የፈጠረና በሁሉ ቦታ ይሚገኝ ፤ የፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ እንደ ተገለጠ መጽሐፍ በመሃል እጁ የሚመለከት ሕያው አምላክ ነው። የሚከተሉት ጥቅሶች የእግዚአብሔር ቃል ስለ እግዚአብሔርና ስለፍጥረቱ ከሚናገረው ምስክርነት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ሥነፍጥረት ሁሉ ስለፈጣሪው የሚናገር እና የሚመሰክር እንደሆነ፤ ሁሉም በዚህ ሕያው አምላክ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ደጋግሞ ያረጋግጣል። ስለዚህም  እግዚአብሔርን ለማወቅ በዙሪያችን ያሉ ሥነፍጥረታትን በትኩረት መመርመር ራሱ በቂ እንደሆነ ይነግረናል።

“--አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤ የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
 
ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፤ የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።
 
የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
 
የሕያዋን ሁሉ ነፍስ የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናት።--” ኢዮብ 12 7-10

“--ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ።
አልፋና ዖሜጋ የመጀመሪያውና የመጨረሻው እኔ ነኝ--” ራእይ 18

ተራራዎችን ከመሥራትህና ዓለምንም ከመፍጠርህ በፊት የዘላለም አምላክ ነህ፤
 ከእንግዲህ ወዲህም የዘላለም አምላክ እንደሆንክ ትኖራለህ” መዝሙር 90 2

አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው።
እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥
እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤
አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም። መዝሙር 10224

እግዚአብሔር ሁሉ የሚቻለው፤ የነበረውን እንዳልነበረ፤ ያልነበረውንም እንዲኖር የሚያደርግ አሐዜ ኵሉ፤ ሁሉን የያዘ፤  ወጣኔ ኵሉ፤ ሁሉን የጀመረ፤የሠራ፤ ፈጻሜ ኵሉ፤ሁሉን የሚጨርስ፤የሚያሳልፍ፤ ከሃሌ ኵሉ ሁሉን የሚችል በአጠቃላይ የሚሳነው ነገር የሌለ ሲሆን ለምን ለመገለጽ ቃላት የማይመጥኑት ኢፍትሃዊ መከራን በፈጠረው ፍጥረት እጅ መቀበልን ወደደ?
“--ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል--” ማቴ. 19፡26

“--ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና--” ሉቃስ 1፡ 37

ከዚህ በላይ የመጻሕፍትን ምስክርነት በከፊል እንዳየነው፤ ኃያልነቱን፤ ምልአቱን፤ ጥበቡን፤ በአጠቃላይ ሁሉን ቻይነቱን ቃላት ሊገልጹት የማይቻላቸው አምላክ ለምን ደካማ ሥጋን ሊለብስና እስከ ሞት ድረስ መከራን ሊቀበል ወደደ ለሚለው ጥያቄ አጭሩ መልስ፤ “የሰውን ልጅ ስለሚወደው፤ ከሚወደው ከሰው ልጅ ያለው ፍቅር ስላስገደደው” የሚል ነው። እውነትም የሰማይና የምድር አምላክ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው ሕያው አምላክ በቅጽበት ኃጢአታችንን ማስወገድ ይችል ነበር፤ ነገር ግን በሥራ እንጂ በቃል መግለጽ ያልፈለገውን ፍቅሩን ሊያሳየኝ ዋጋ ሊከፍልልን ወደደ ይህ የእርሱ ውሳኔ ነው። 

ስለ እኛ የደረሰበትን የመከራ ዝርዝር በተመለከተ እኛ በምናውቃቸው ቃላት ብቻ በከፊል በጣም ጥቂቱን ለመናገር ያህል እንጂ በቃላት ሊመጠን የሚችል አይደለም። አምላክ በሥጋዌ ወደዓለም መጥቶ መከራውን ከመቀበሉ በፊት ቅዱሳን ነቢያት ራሱ በሰጣቸው የትንቢት መነጽር ሲመለከቱትና ሲተርኩት ኑረዋል። ከብዙዎቹም መካከል ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው ይተነብይ ነበር።

 “--በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታበእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።  እርሱ ግን ስለ መተላለፋችንቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱአዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። 
ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝምእንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአትተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? ትንቢተ ኢሳይያስ--” 53፡4-8

ቃላት የማይወስኑትን መጠነ ሰፊ መከራን ይቀበል ዘንድ ያስገደደው “ፍቅር” እንደሆነ ተመልክተናል። ለመሆኑ ፍቅር ምንድነው? ለዚህ ዓይነቱ ፍቅር መገለጥስ ምክንያቱ ምን ነበር?
ፍቅር መውደድ ነው መውደድስ ምንድነው ? ቢባል
ፍቅር በግእዝ ሲሆን በአማርኛ መውደድ ማለት ነው?
ፍቅር በወል ሲገለጽ በዙ ቅጽሎች ወይም ገላጮች አሉት። እነዚህም፤

·         የእግዚአብሔር ፍቅር (እግዚአብሔር ለሰው ያለው ፍቅር)
·         ሰው ለአምላኩ ያለው ፍቅር
·         የተቃራኒ ጾታ ፍቅር
·         የወላጅ ፍቅር
·         የቤተሰብ ፍቅር
·         የሐገር ፍቅር
·         የገንዘብ ፍቅር
·         የዝሙት ፍቅር
·         የራስ ፍቅር
ወዘተ የሚባሉት ናቸው። ከዚህም ሌላ ብዙ መተንተን ይቻላል። መሠረታዊ ነጥቡ ግን ትክክለኛው ፍቅር የትኛው ነው? የሚል ነው።

የፍቅር ወይም የመውደድ ትክክለኛ ትንታኔው ምንድነው ስንል ፍቅር በሥራ የሚታይ እንጂ በቃላት የሚገለጽ አይደለም የሚል ነው። በዚህም ፍቅር ጣፋጭ አነጋገር ሳይሆን ጣፋጭ ሥራ ነው ይባላል። ይህ  አባባል እውነት ቢሆንም ግን በሰዎች አስተሳሰብ የምንሰጠው ትንታኔ አለ። ይኸውም
ፍቅር ሳይቀበሉ መስጠት ነው፤

ፍቅር መመዘኛ መለኪያ ሳያስፈልግ በነጻ ለሌላው ገንዘብን፤ ጉልበትን፤ ጊዜን፤  ሕይወትን፤ እንኳን ሳይቀር አሳልፎ መስጠት ነው፤
ማለትም አንድን ሰው ሴትም ትሁን ወንድ ለመወደድ መልካም ጠባይ፤ ቀና አመለካከት፤ መልካም ሥነ ምግባር ግዴታ አይጠበቅባቸውም። 

·         መልከኛ
·         ሐብታም
·         ለጋስ
ወዘተ መሆንም እነርሱን ለመውደድ እንደ ሚዛን የምንጠቀምባቸው አይደሉም።
ተጨባጩን ነገር፤ በሕይወታችን አዘውትረን የምናየውን እና የምንኖረውን እውነት ስንናገር ግን
በሰዎች ህይወት ውስጥ ፍቅር ምክንያት አለው። በተለይ አሁን በደረስንበት ዘመን፤ ሰው ሰውን የሚወደው
በዝምድናው ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን፤ ልጆች ወላጆቻቸውን ወይንም ከሚደረግላቸው የቅርብ እንክብካቤና ስጦታ በመነሳት የቅርብም ሆነ የሩቅ ዘመዶቻቸውን ይወዳሉ።
·         በጠባይ፤
 በጠባዩ የማይጎረብጥ፤ የማይነጫነጭ፤ የማይከራከር እንዳሉት፤ ወይም እንዳዘዙት፤ እንደ ነዱት የሚሄድ ሰው ከተገኘ ለመሳሪያነት ይወደዳል
·         በመልክ
በመልኩ ወይም በመልኳ በመሳሳብ ለሥጋዊ ፍላጎት መዋደድ አለ።
·         በልግሥና
(በሚደረግለት የጥቅም መጠን) በነዚህ ምክንያቶች ፍቅር ይመሠረታል። 

ወይም ልባዊ ያልሆነ ፍቅር ከፍርሃት ከጥቅም ወዘተ የተነሣ በሥልጣን በሐብትና በመሳሰሉት ደግሞ ሰው ሰውን ፈርቶ አማራጭ ስለሌለው እንደ ወዳጅ አፍቃሪ መስሎ እየተገዛ ሊኖር ይችላል።

በነዚህ ሁሉ የሚመሠረት ቀረቤታና መቀራረብ መረዳዳትም እንዲሁም ትክክለኛ ብለን የምንጠራው የፍቅር ዓይነት፤ ሁሉ በይዘት አንዱ ከሌላው ባይመሳሰልም በስያሜው ግን ስሙ ያው “ፍቅር” ይባላል።

 እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያለው ፍቅር ግን ከዚህ ሁሉ የተለየ ፍቅር ነው። ምክንያቱም ፍቅሩን ለሰው ልጅ የገለጠው ሰውን ሳይፈጥር አስቀድሞ ነው። ይህ ማለት ሰው አምላኩን ማመስገን እንኳን ሳይጀምር ነው። ምክንያቱም አልነበረም። የእግዚአብሔር ፍቅሩ “እወድሃለሁ ወይም እወዳችኋለሁ” በማለት በቃል ብቻ የተመሠረተ ወይም የተገለጸ አልነበረም ፤ የገለጠው” በሥራ ነበር ፡
ፍቅር ተብሎ የሚጠራው፤ ፍቅር የባሕርዩ የሆነ፤ ፍቅርን በሥራ ያሳየን የእግዚአብሔር ቃሉና ልጁ የዓለም መድኃኒት መድኃኔ ዓለም  ከሁሉ የሚበልጠው የፍቅር ዓይነት የቱ እንደሆነ ሲነግረንና እኛም እርሱ በወደደን መጠን በዚሁ ዓይነት እንድንከተለው እንዲህ ይለናል።

“--እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። 
ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት የላቀ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” ዮሐ. 15፡12-14

እግዚአብሔር ለሰው የነበረውና ያለው ፍቅር የጀመረው ከሥነ ፍጥረት የአፈጣጠር ታሪክ ጋር ተያይዞ ነበር። ይህም ዓለምን ወይም ሥነፍጥረትን ከዕለተ እሁድ ጀምሮ እስከ ዕለተ አርብ ድረስ ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ማለት ነው የአፈጣጠሩ ሁኔታ የተለየ መንገድ ነበር። ማለትም በቃሉ ብቻ ይሁን በማለት ነበር። 

በኋላም የፈጠረውን ሁሉ ዐየና ሁሉም መልካም ነው አለ። ያ መልካም የሆነው ሁሉ የተፈጠረውም በመልኩና ብምሳሌው ለሚፈጥረው ለሰው ልጅ አገልግሎትና መገልገያ ነበር። ለሰብአዊ ፍጡር የተደገሰ ድግስ፤ የፍቅር ግብዣ ነበር። ከዚያ በኋላ ተጋባዡን በልዩ ጥበብ ፈጠረው።  “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምላሊነ”። የሰው ልጅ በምድራዊው ሕይወቱ ሁሉ ሊጠቀምባቸው ሕይወቱን ይመራባቸው ዘንድ ለሕይወቱ መሠረታውያን የሆኑትን ሁሉ
·         ምግብን
·         መጠጥን
·         ልብስን
·         የሚኖርባት ውብ የሆነች ቦታን
ሁሉ ፈጥሮ አዘጋጅቶ እንደ ልባዊ አፍቃሪ በተሟላ ግብዣ ሰውን በመልኩ ፈጠረው፤ ወደ ግብዣው ጠራው፤ ያዘጋጀለትንም ሁሉ ሰጠው።

በማንም ፍጥረት ላይ ወይም ለማንም ፍጥረት ከእሁድ እስከ ዓርብ በቃሉ ብቻ ለፈጠራቸው ፍጥረታት ያልተናገረውን ተናገረ እና አደረገው “ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ” ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር አለ።

ሁሉን ብላ፤ ሁሉን ግዛ፤ ብሎ ስልጣንን እና ባለቤትነትን በገፍ ሰጠው፤ ብዛ ተባዛ ብሎም መረቀው፤ አንዲት ምልክትን ብቻ በትእዛዝነት ሰጠው ይህች ምልክት እግዚአብሔር ፈጣሪ፤ ሰው ደግሞ ፍጡር መሆኑ የምትገልጽ ማለትም ሰው ለፈጣሪው ታዛዥነቱን የሚያሳይባት አንዲት ትእዛዝ ብቻ ነበረች። 

ሁሉንም ትበላለህ ሁሉንም ትገዛለህ፤ “መልካምና ክፉን የምታስታውቀውን ዛፍ ግን” አትበላም። እሷን በበላህ ጊዜ ሁለት ሞትን ትሞታለህ በማለት ግልጽ አድርጎ አስረዳው። ከዚያ ውጭ የተፈጠረው ሁሉ ያለምንም ገደብ ተሰጠው፤ በፍጥረት ሁሉ ላይ ንጉሥ ሆኖ ተሾመ፤ ከርሱ በላይ የዘላለም ንጉሥ መኖሩን ያውቅ ዘንድ ግን እንደ ምልክት፤ እንደ ማስገንዘቢያ ትሆነው ዘንድ ገደብን አደረገለት። 

ከተሰጠው ገደብ አልፎ አምላክነትን ሲሻ የተዋረደው ዲያብሎስ(ሳጥናኤል) ከክብሩ ተራቁቶ ባዶውን ቀርቶ ብቸኛ ስለነበረ ከርሱ ጋር አብሮ የሚወድቅ የሚዋረድ ይፈልግ ነበር።

ሰው የተፈጠረው በወደቀው በሳጥናኤል ቦታ ነበር። ማለትም መላእክት በ100 ነገድ የተከፈሉ ነበሩ 100ኛው ነገድ አንዱ የሳጥናኤል ነገድ ስለወደቀ ሰው ከ99ኙ ነገድ 100ኛ ሆኖ የተፈጠረ ነው። ስለዚህ ዲያብሎስ በሰው ልጅ ላይ ከባድ ቅንአት ነበረበት አለበትም። ሰውን ከአምላኩ ጋር አጣልቶ እንደ እርሱ እንዲዋረድ እጅግ ይፈልጋል። በመሆኑም 

ሁሉንም ሰጦሃል፤ ስልጣኑም፤ ሐብቱም፤ ሁሉ በገፍ ተሰጥቶሃል፤ ነገር ግን አንዲት የዛፍ ፍሬን ብቻ ለምን ከለከለህ? ለምን ይመስልሃል? ያልተሰጠህ፤ ያልተፈቀደልህ የዚች ዛፍ ፍሬ ብቻ ነው። ለምን? ምክንያቱ ግን ይህቺን የዛፍ ፍሬ በበላህ ጊዜ አምላክ ትሆናለህ። የአምላክነትን ምስጢር ይዛለች። ለዚህም ነው እግዚአብሔር እንደሱ አምላክ እንዳትሆን የከለከለህ በማለት መከረው።
የአዳምን የትዳር ጓደኛ ሔዋንን በማታለል አሳምኖ የተከለከለቺውን ፍሬ አስበላቸው።

አምላካዊ ቃል አይታበልም እና የአምላክ ውሳኔ መፈጸም ነበረበት ስለዚህ የታዘዙትን አንድ ትእዛዛ ማክበር ባለመቻላቸው ለብዙ ትእዛዛት ተዳረጉ። ከክብራቸው ተዋረዱ፤ ወደቁም።  ክብራቸውን አጡ። ሁለት ሞትን ሞቱ። ሞተ ሥጋን እና ሞተ ነፍስን ሞቱ ከአምላካቸው ተለዩ፤ ራቁታቸውን ቀሩ። ዲያብሎስ እንዳለው ግን አምላክ መሆን አልቻሉም። እንዲያውም ሰብእናቸውንም አጡ፤ ከዚያች የክብር ቦታቸው በመላእክት እየተገፈተሩ ወጡ። ይህ ከዛሬ 7507 ዓመታት በፊት ነበረ።

አዳምና ሔዋን ከብዙ ርግማንና ሥቃይ በኋላ በደላቸውን አምነው ወደ አምላካቸው ጮሁ፤ ይቅርታን ጠየቁ፤ በንስሃ ተመለሱ። ንስሃን የሚቀበል አምላክም መቸም ቢሆን የማይደበዝዘው ፍቅሩ እንዳለ ሆኖ ንስሃቸውን ሰማና ከ5500 ዓመታት በኋላ ከልጅ ልጃቸው ተወልዶ እንደሚያድናቸው ቃል ገባላቸው። 

“በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ፤ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ”=አምስት ሺ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጀ በመስቀል ላይ በሚደረግ ሞቴ አድንኃለሁ።

አዳምና ሔዋን የተሰጣቸውን ክብር ቢያውቁበት ኖሮ ሞተሥጋም ሆነ ሞተነፍ አይኖርም ነበር። ሕያዋን እንጂ ሙታን የሚል ስያሜ ለሰብአዊ ፍጡር አይሰጥም ወይም አይኖርም ነበር። ነገር ግን ሰው ክብሩን አላወቀም። ያለምንም ምክንያት ያፈቀራቸውን አምላክ ካዱት፤ ከጠላት ጋር ሆነውም በአምላክነቱ ተነሡ።

ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ ዲያብሎስ በፍጥረት ላይ ነገሠ። ከመጀመሪያዎቹ ከአቤልና ከቃኤል ጀምሮ እርስ በርስ መገዳደል ተጀመረ፤ ሰዎች በኃጢአታቸው አስከፊ በሆነው በውሀ መደምሰስን ጨምሮ ብዙ ልዩ ልዩ ሥጋዊ መቅሰፍትም ደረሰባቸው፤
ነቢዩ ዳዊት የሰውን ሁኔታ ሲገልጽ “ ሰው ክቡር ሆኖ ተፈጥሮ ነበር ነገር ግን ክብሩን አላወቀም አላወቀበትም “ ከሰውነት ወጥቶ እንደ እንሥሳ ሆነ” ይላል። የያዙትን አለማወቅ ታላቅ ችግር ነው። ምክንያቱም ካላወቁት አያከብሩትም፤ ካላከበሩት ይጥሉታል። ክብርን መጣል ደግሞ ራስን መጣል ነው። ያውም ከአምላክ የተሰጠ ክብር!  

 ከዚያ ሁሉ ውድቀት በኋላ ግን አምላክ በማይሻረው ቃሉ እንደ ተናገረው በሰው ልጅ ላይ የደረሰው ሁለት ሞት ነበር። አንዱ የሥጋ ሲሆን ሌላው በነፍስ ለዘላለም ያለገደብ መሞት ነው። ይህ ደግሞ የደረሰው በአዳም እና በሔዋን ብቻ ሳይሆነ በሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ላይ ነበር። በመሆኑም በሰብአዊ ፍጡር አለመታዘዝ የመጣው የዘላለም ሞት ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ በውርስነት የሚተላለፍ ስለነበረ ይህንን ሞት መሻር ያለበት የዚህ ተላላፊ ኃጢአት ወራሽ የሆነ ሰብአዊ ፍጡር ሳይሆን ሕያው አምላክ ብቻ ነበር። 

ዘመኑ እየቀረበ ሲሄድ ከዛሬ 2700 ዓመታት በፊት በነቢዩ በኢሳይያስ እና በሌሎቹም በነቢያት አንደበት የአምላክ የፍቅር ሥራ የመከራው ዓይነትና የፍቅሩ አገላለጽ ተነገረ ተተነበየ። አንዱን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፡ “ድንግል በድንግልና ጸንሳ በድንግልና ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ ትለዋለች፤ እርሱም ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል” ኢሳይሳ 7፡ 14። ይህ ከድንግል 

የሚወለደውም ብርሃን እንደ ሆነ ይህ በኃጢአት የጨለመውን የሥነፍጥረት ሕይወት ሁሉ በብርሃን እንደሚለውጥ ተናገሩ።
“ከእግዚአብሔር በቀጥታ የተላከው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል የተመረጠቺውን ድንግል አበሠራት፤ በሥነ ፍጥረት ታሪክ ውስጥ ተደርጎ ተፈጽሞ የማያውቅ ልዩ  ዜናን ነገራት፤ ድርጊቱ በተፈጥሮ ህግ ሊደረግ የማይችል ቢሆንም “ ለሕያው አምላክ ግን የሚሳነው የለም “ በማለት አብራርቶ አራቆ ነገራት፤ ምርጫዋን ዕድሏን ደስይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ በማለት መላልሶ አረጋገጠላት፤ የአምላክ ወደ ዓለም መምጣት ይፋ ሆነ ።

 ሕይው አምላክ በማይመረመር ፍቅሩና ጥበቡ ከሥጋችን ሥጋን ከነፍሳችን ነፍስን ነሥቶ በፍጹም ተዋሕዶ ተጸነሰ፤ ጠባቂዋ ዮሴፍ በሁኔታው ቢደናገጥም፤ እንደ ሰብአዊነቱ እንዳይታማ ፈርቶ ለመሸሽ ቢያስብም አሁንም የእግዚአብሔር መልአክ የነቢዩን ትንቢት እየጠቀሰ የተደናገጠውን ቅዱስ ዮሴፍን የዳዊት ልጅዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድአትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስትለዋለህ።  በነቢይ ከጌታ ዘንድ። እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንምአማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔርከእኛ ጋር የሚል ነው” እያለ አስተማረው አጽናናው። ማቴዎስ 1፡20-23

 “--የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውንልጁን ላከ--” ገላትያ 4፡4
ይህም በ5500ዓ/ዓ ፍጻሜ አካባቢ ላይ ነበር)
የሁላችንን በደል ሊከፍል በፍቅር ተገዶ ወደ ዓለም የመጣው አምላክ ከጽንሰቱ ጀምሮ ተንገላታ የሚያስተናግደው አንድ ሰው፤ የሚጠጋበት አንድ ቤት ባለመገኘቱ በከፍቶች በረት ውስጥ ተወለደ ። በዚያም እንሥሳትን ጨምሮ ፍጥረታት ሁሉ አመሰገኑት፤አገለገሉትም።

መላእክትና ሰዎች የሰላምን መዝሙር እየዘመሩ ለሰላም የመጣ ሰላምን ለዓለም የሚያድል የሰላም ንጉሥ መወለዱን እየገለጹ ዘመሩለት። በዚህም የሰላሙ መሠረት ተጣለ፤ ወይም ተመሠረተ። የጥበብ ሰዎች የእጅመንሻ ስጦታን አበረከቱለት። 

ኃያላንን ሁሉ በቅጽበት ውስጥ እንዳልነበሩ ማድረግ ሲችል በፈቃዱ ብቻ ከፈጠረው ከሰውልጅ ፊት ሸሽቶ በግብጽ ምድር በስደት ተንከራተተ፡፡ ሁሉን ማድረግ ሲቻለው እንደ ሕጻናት ጥቂት በጥቂት አደገ። በ30 ዓመቱ በማየ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ በትሕትና ተጠመቀ። ይህም ከ26-30ዓ/ም ባለው ጊዜ ነበር (4 ዓመት ወደኋላ የታለፈ ጊዜ አለ)። 40 ቀንና 40 ሌሊት  ጾመ፤ እኛን ከፈተና ለማውጣት እርሱ በዲያብሎስ ተፈተነ። ከ26-30 ዓ/ም ባለው ጊዜ።

ወንጌልን የመስበክ ሥራውን ጀመረ። 12ቱን ሐዋርያት መረጠና ዓለምን ያንጹ፤ የምሥራቹን ያወሩ ዘንድ ከ3 ዓመታት በላይ አሰለጠናቸው። ከመረጣቸው፤ ካስተማራቸው፤ ቸርነቱንና ፈዋሽ የሆነውን ቅዱስ ቃሉን እየተመገቡ አብረውት ከኖሩ ደቀመዛሙርቱ መካከል ልቡናው የጭንጫ መሬት የሆነበት አንዱ ይሁዳ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ጋር ተሻርኮ በ30 ብር ሸጠው። አሳልፎም ለጨካኞች ሰጠው።

ምንም እንኳን ሰዎች ምክንያት ቢሆኑም ቅሉ በማዳን ሥራው በሆነው ነገር ሁሉ በፍቅሩ ብዛት ራሱን በፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ እንጂ በሰዎች ኃይል በሽንፈት ተገዶ የተወሰደ ወይም ተጎትቶ የተሰጠ አይደለም። ይህንን ራሱ እንደሚከተለው ገልጾታል።
“ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና ስለዚህ አብ ይወደኛል። እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችንትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ”። ዮሐንስ 10፡ 18

ሰዎች ግን የትንቢቱ ምክንያቶችና መሣሪያዎች ነበሩ። “የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤  ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ” ማቴዎስ 26።

በመሆኑም ከጌቴሴማኒ የጸሎት ጊዜ በኋላ በደቀመዝሙሩ በይሁዳ እጅ ተላልፎ ከተሰጠና ከተያዘባት ቅጽበት ጀምሮ ወደ ልዩ ልዩ የቤተ አይሁድና የሮማውያን ችሎትና ባለሥልጣናት ፊት ቀረበ። የሐሰት ምስክሮች በገንዘብ ተገሥተው መሰከሩበት። የሮማ ወታደሮች አንገላቱት ካህናትና ሊቃነ ካህናት፤ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ዘበቱበት። መጀመሪያ ወደ ሊቀካህናቱ ወደ ሀና፤ ከዚያም ወደ ቀያፋ፤ ተወሰደ። ተከታዮቹም ተበታተኑ። ማቴዎስ 26÷31፤56

መቸም ቢሆን አልለይህም አልከዳህም እያለ ሲምል ሲገዘት የነበረው ደቀመዝሙሩ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ እንኳን ለዓይን ዕይታ ከሚዘገንን የመከራ ብዛት የተነሣ ስለፈራ ሦስት ጊዜ በተከታታይ “አላውቀውም” በማለት ካደው።

የካህናቱ ጉባኤ ወደ ጲላጦስ ላከው፤ ጲላጦስም፤ ወደ ሄሮድስ፤ ሄሮድስም እንደ ገና ወደ ጲላጦስ መለሰው። በዚህ ሁሉ መካከል የደረሰበትን የመከራ ዓይነት፤ክብደትና ብዛት ለመግለጽ የሚችል አንደበት፤ የመከራውን ጥልቀት የሚያስረዱ ቃላት አልተገኙም፤ የሉም፤ አይገኙምም። በዚህ ሁሉ በአንደበቱም ሆነ በሥራው አንድም እንኳን ስህተት አልተገኘበትም። ባለሥልጣናቱ ሁሉ “ምንም ስህተት አላገኘንበትም” በማለት ተናግረውለታል። ቤተ አይሁድ ግን እርሱ ካልተወገደ  እረፍት የለንም አሉ። ስቀለው፤ ስቀለው፤ በማለትም ጭሆትን አበዙ።በመጨረሻም ጲላጦስ “ከደሙ ንጹህ ነኝ” በማለት እጁን ታጥቦ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው።
ነቢዩ ዳዊት በትንቢቱ በትንቢቱ የተመለከተውን ስለክርስቶስና ስለተፈጸሙበት ኢፍትሃዊ ሥራዎች ሲናገር

“ተንሥኡ ላዕሌየ ሠማዕተ ዐመፃ፣ወዘኢየአምር ነበቡ ላዕሌየ፣”
የክፋት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ። 
 
ስለ በጎ ክፋትን መለሱልኝ፥ መዝሙር 35፡11

“ዐገቱኒ ከለባት ብዙኃን፡፡ ወአኀዙኒ ማኅበሮሙ ለእኵያን”፡፡ =

ብዙ ውሾች ከብበውኛልና፤ የክፋተኞች ጉባኤም ያዘኝ፤ እጆቼንና እግሮቼን ቸነከሩኝ። አጥንቶቼሁሉ ተቈጠሩ፤ እነርሱም አዩኝ ተመለከቱኝም።  ልብሶቼን ለራሳቸው ተከፋፈሉ፥ በቀሚሴም ላይዕጣ ተጣጣሉ።  መዝሙር፡ 21(22) 16-18

ቀነዉኒ እደውየ ወእገርየ፡፡ ውኆለቁ ኵሎ
                  አዕጽምትየ፡፡(እጆቼንና እግሮቼን በሚስማር ቸነከሩ አጥንቶቼንም ቆጠሩ)

“ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ ፤ ወአስተዩኒ ብሒዐ ለጽምዕየ፤ =
ለመብሌ ሐሞትን ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤን አጠጡኝ። (መዝ.6921)


የክርስቶስን መከራ አራቱ ወንጌላውያን ጽፈውት ይገኛሉ። በዚህ ዝግጅቴ የማቴዎስን ወንጌል ብቻ እንመለከታለን። የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 26 እስከ 28።

በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥ ኢየሱስንምበተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤ ነገር ግን። በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን አሉ። 

በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ። ሲበሉም። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተአንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ።  እጅግም አዝነው እያንዳንዱ። ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንንይሉት ጀመር።  እርሱምመልሶ። ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው። የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤  ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ። 

አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ። መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንንአለ፤ አንተ አልህ አለው።  ሲበሉም ኢየሱስእንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።  ጽዋንምአንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤  ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስየአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው። 

በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚልተጽፎአልና፤  ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።  ጴጥሮስም መልሶ። ሁሉም በአንተቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው።  ኢየሱስ። እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜትክደኛለህ አለው።  ጴጥሮስ። ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀመዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ።  በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣደቀ መዛሙርቱንም። ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው። 

ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር።  ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግአዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው።  ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ። አባቴ፥ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ። 

 ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን። እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳልትተጉ አልቻላችሁምን?  ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነውአለው። 

 ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና። አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁንአለ።  ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው።  ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ።  ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ እነሆ፥ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።  ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝቀርቦአል አላቸው።  

ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘውከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ።  አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ብሎምልክት ሰጥቶአቸው ነበር። ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎሳመው። 

 ኢየሱስም። ወዳጄ ሆይ፥ ለምን ነገር መጣህአለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነውያዙት።  እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶጆሮውን ቈረጠው።  

በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው። ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራውመልስ።  ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝየማይቻል ይመስልሃልን?  እንዲህ ከሆነስ። እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ? 

 በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን?በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም።  ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነየነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።  

ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት።  ጴጥሮስ ግንእስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋርተቀመጠ። 

 የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥አላገኙም፤  ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም።  በኋላም ሁለት ቀርበው። ይህ ሰው።የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሎአል አሉ።  ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ።እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን አለው።

 ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረንበሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው። 

 ኢየሱስም አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይምደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው።  በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ። ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮችስለ ምን ያስፈልገናልእነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋልአለ።  እነርሱም። ሞት ይገባዋልብለው መለሱ።  

በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጐሰሙትም፥ ሌሎችም በጥፊ መትተው። ክርስቶስ ሆይ፥ በጥፊ የመታህ ማንነው?  ትንቢት ተናገርልን አሉ።  ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱቀርባ። አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።  እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉፊት ካደ።  ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት።

ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች።  ዳግመኛም ሲምል። ሰውየውን አላውቀውም ብሎካደ።  ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን። አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞከእነርሱ ወገን ነህ አሉት።  በዚያን ጊዜ። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውምዶሮ ጮኸ።  ጴጥሮስም። ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭምወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።

 ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤  አስረውም ወሰዱት፥ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበትአይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ።  ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴበድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶንአንተው ተጠንቀቅ አሉ።  ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደናታንቆ ሞተ። 
የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው። የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደምአሉ።  ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት።  ስለዚህ  መሬት እስከ ዛሬ ድረስየደም መሬት ተባለ። በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ። 

 ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህንብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም። አንተ አልህአለው።  የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም።  በዚያን ጊዜ ጲላጦስ። ስንት ያህልእንዲመሰክሩብህ አትሰማምንአለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳአልመለሰለትም።  በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው።  
በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው።  እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ።በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁአላቸው፤  በቅንዓትአሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።  እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ። ስለ እርሱ ዛሬ በሕልምእጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት።  

የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ።  ገዢውምመልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁአላቸው፤ እነርሱም። በርባንን አሉ።  ጲላጦስ። ክርስቶስየተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገውአላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ።  ገዢውም። ምን ነው?ያደረገው ክፋት ምንድር ነውአለ፤ እነርሱ ግን። ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።  ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመርእንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። 

እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ።  ሕዝቡም ሁሉመልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ።  በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ።  

በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱአከማቹ።  ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥  ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃአኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤  ተፉበትምመቃውንም ይዘው ራሱን መቱት።  ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትምወሰዱት።  

ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።  ትርጓሜውየራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥  በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም።  

ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥  በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር።  ይህ ኢየሱስ የአይሁድንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ።  በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራከእርሱ ጋር ተሰቀሉ።  የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና።  

ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀልውረድ አሉት።  እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህአሉ።  ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛምእናምንበታለን።  በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁንያድነው።  ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር።

  ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።  በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ።ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝማለትነው።  በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ።  ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው።  ሌሎቹ ግን። ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነውእንደ ሆነ እንይ አሉ።  ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ። 
 እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችምተሰነጠቁ  መቃብሮችም ተከፈቱ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ  ከትንሣኤውም በኋላከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።  የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስንየሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው። ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ።

 ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤  ከእነርሱም መግደላዊትማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።  በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤  ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦየኢየሱስን ሥጋ ለመነው።  ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታከፈነው፥  ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎሄደ።  መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ።  

በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና።  ጌታሆይ፥ ያአሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።  እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱመጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅየከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት።  ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩንአስጠበቁ።

 በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። 
እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ።  

መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ።  ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ።  መልአኩምመልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤  እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ።  ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀመዛሙርቱ ንገሩአቸው።  እነሆም፥ ነገርኋችሁ።

 በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ።  እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና። ደስ ይበላችሁአላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት።  በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው። 
ሲሄዱም ሳሉ እነሆ፥ ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ።  ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበውተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው። እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ።  ይህም በገዢውዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን አሉአቸው።  እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደአስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል። 

 አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥  ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ።  ኢየሱስምቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።  እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።

ሰባቱ የክርስቶስ የመጨረሻ ቃላት/አጽርሐ መስቀል

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላትና ሁላችንም በልቡናችን ሰሌዳ ልንጽፋቸው የሚገቡ አደራዎች።

1.      “--ይቅር በላቸው--”
2.     “--ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ--”
3.     “--እነሆ ልጅሽ--”
4.      “--አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ?--”
5.     “--ተጠማሁ--”
6.     “--ተፈጸመ አለ--”
7.   “--አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ--”

የሚሉት ሲሆኑ ሙሉ ዐረፍተ ነገራቱን እንደሚከተለው አነባቸዋለሁ።

ኢየሱስም። አባት ሆይ፥ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው አለ። ሉቃስ 23፡34

ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው። ሉቃስ 23፡43

ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን።
 አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀመዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት። ዮሐንስ 19፡26

በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው። ማቴዎስ 27፡ 46

ከዚህ በኋላ ኢየሱስ፡ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ። የሐንስ 19 ፡28

ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ። ዮሐንስ 19፡30

ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ። አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ አለ። ይህንም ብሎ ነፍሱንሰጠ። ሉቃስ 23፡46

መድኃኔዓለም ክርስቶስ በቀራንዮ በመስቀላይ ሁሉም ተፈጸመ በማለት ሕያዊት ነፍሱን ከሰጠ በኋላ በምድር ላይ 4 በሰማይ 3 ተአምራት ታዩ። ለፈጠራቸውም መሰከሩ፤ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ሥነፍጥረት ምስክርነታቸውን ተቀብለው “እውነትም የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” በማለት አመኑበት።

1.      የቤተ መቅደስ መጋረጃ ለሁለት ተከፈለ
2.     መሬት ተነዋወጠች
3.     አለቶች ተሰነጣጠቁ
4.     መቃብራት ተከፍተው ሙታን ተነሱ
5.     ፀሐይ ጨለመች
6.     ጨረቃ ድም ሆነች
7.     ከዋክፍትም ረገፉ።
ሥነ ፍጥረት ሁሉ የእጁ ሥራ ስለሆነ የፈጣሪውን ክብር ለመግለጽ ሁሉ በበኩሉ ኃይሉን ያሳያል ።
በሌሊት በቤተልሄም ሲወለድ ሌሊቱ ወደ ቀን ተለወጠ፤ በቀን ሲሰቀል ደግሞ ቀኑ ወደ ሌሊት ተለወጠ።

እኛን ከዘላለም ሞት ለማዳን ብቻ መከራ የባሕርዩ ያልሆነ ሕያው አምላክ መፈቀር ሳይገባን በነጻ ያለምንም ምክንያት እንዲሁ እስከ መጨረሻው ወደደን። እንደ ሥራችን ግን የምንወደድ አልነበርንም። ምክንያቱም፡
ከመጀመሪያዋ ቅጽበት ጀምረን ከጠላት ዲያብሎስ ጋር ተሻርከን በአምላክነቱ ተነሣንበት፤ በኋላም እኛን እየፈለገ ወደ እኛ ሲመጣ ከጽንሰቱ ጀምረን ያሳደድነው እኛው ነን፤
በየደረሰበት ስናሳድደው፤ ስናሳጣው፤ የነበር እኛው ነን፤ በ30 ብር አሳልፈን የሸጥነው እኛው ነን፤
በሐሰት የመሰከርንበት፤ያንገላታነው፤ ያፌዝንበት፤ ምራቃችን የተፋንበት፤ ያቃለልነው፤ እኛው ነን፤
በሚስማር የቸነከርነው፤ የሰቀልነው፤ ጎኑን የወጋነው፤ በመጨረሻም በመስቀል የሰቀልነው እኛው ነን። ሌላ ማነው? እንሥሳት ወይም እጸዋት አይደሉም። እኛ ብቻ ነበርን። እሱ ግን ወዳጆቼ እያለን ስለ እኛ ሕይወቱን በመስቀል ላይ ሠዋልን። 
ታዲያ ከዚህ የሚበልጥ ምክንያት የሌለው ፍቅር የታለ?
በተፈጥሮ ታሪክ ውስጥ በማንም ላይ ያለደረሰ ዘርፈ ብዙ መከራ ደረሰበት፤ በመጨረሻም በቀራንዮ አደባባይ በሽፍቶ መካከል ተሰቀለ፡፡

ከቀኑ በ6 ሰዓት ሰቀሉት፤ በ9ሰዓት ነፍሱ ከሥጋው ተለየች ፤በ11 ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው በጎልጎታ ቀበሩት
ዓርብ ለቅዳሜ አጥቢያ በ11 ስዓት በአካለ ነፍስ ወደሲኦል ወርዶ ሲኦልን ባዶዋን አስቀራት አዳምንና ዘሩን ወደነበረ ክብራቸው መለሰ፤ እኛን መለሰን።

 በሦስተኛው ቀን ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ሞትን ድል አድርጎ ዲያብሎስን በማይፈታ ሥልጣን አሥሮ የሰውን ልጅ ነጻ አውጥቶ መግነዙን ፍቱልኝ መቃብሩን ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ በድል አድራጊነት ተነሣ። ከዚች ቅጽበት ጀምሮ ሰላም ሆነ፤ ሰላም ታወጀ፤ ዲያብሎስና ሞት ተሻሩ፤ አዳምና ዘሩ ነጻ ወጡ፤ ገነትና መንግሥተ ሰማያት ለሁላችን ክፍት ሆኑ። ሲኦልና ገኃነም ተዘጉ።
“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በአቢይ ኃይል ወስልጣን፤ አሰሮ ለሰይጣን፤ አግአዞ ለአዳም፤ እምይእዜሰ፤ ኮነ፤ ፍስሃ ወሰላም” ተባለ።

በመከራውና በሞቱ ያዘኑትን፤ የተከዙትን ከመግደላዊት ማርያም ጀምሮ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትን ጨምሮ እየተገለጸ አረጋጋቸው። ድል አድራጊነቱን በግልጽ አሳየ፤ አረጋገጠ፤ የመጨረሻ መመሪያዎችንም አስተላለፈ። ያሰለጠናቸውን የማይሻር ሥልጣንን አስታጥቆ ወደ ዓለም ላካቸው፤ ለዘላለም ከተከታዮቹ እንደማይለይም ቃል ገባላቸው። 

በድል አድራጊነት በተነሣ በ40ኛው ቀን በ34ዓ/ም በደብረ ዘይት ተራራ በኩል ቅዱሳን ሐዋርያት እያዩት በደመና ተከቦ የ10 ቀናት የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ በመስጠት በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ አረገ።

በማይዛባውና በማይሻረው ቃሉ በተስፋው መሠረት በ10ኛው ቀን (በተነሣ በ50ኛው ቀን፤ ባረገ በ10ኛው ቀን) በ34ዓ/ም መንፈስ ቅዱስን ላከላቸው። 

አሁንም በሕያው ቃሉ እንደተናገረ በግርማ መለኮቱ ተመልሶ ይመጣል። ለዚያያን ጊዜው የክብር ትንሣኤ ያብቃን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን

No comments:

Post a Comment