የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ክፍል 18
ይህ ትምህርት የክፍል 18 ትርጎምና ማብራርያ
ነው።
በዚህ ዝግጅቴ
ሁለት የተለያዩ ትርጉሞችን በመጠቀም ክፍል 18ን ለማብራራት እሞክራለሁ
። በንቃትና በትጋት እንድንከታተል እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን። አሜን!
1ኛው የትርጉም ዓይነት “የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም” በቅደም
ተከተላቸው የሚለው ሲሆን ይህ ትርጉም በቀላሉ “የቃላት ትርጉም” ሊባል ይችላል።
2ኛው የትርጉም ዓይነት “የዐረፍተ ነገር
እና የይዘት ትርጉም” የሚለው የአተረጓጎም ዓይነት ደግሞ “የይዘት ትርጉም” ልንለው
እንችላለን።
ይህ አተረጓጎም የቃላቱን መሠረታዊ ትርጉም ሳይለቅ አቀማመጣቸውን ሊቀይር
ይችላል፤ ለአማርኛ አነጋገር ተስማሚ የሆነ የቋንቋ ውበትን በመጨመር አስተካክሎ የመፍታት ወይም የመተርጎም መንገድ ነው።
ይህ አተረጓጎም የትርጉም ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት ትክክለኛ የአተረጓጎም
መንገድ ነው። ይህ ማለት የቋንቋ ችሎታችን እያደገ በሄደ ቁጥር አንድን ቋንቋ ስንተረጉም ማለትም ለምሳሌ ከግሪክኛ ወደ አማርኛ
መተርጎም ብንፈልግ የግሪከኛውን ትክክለኛ ትርጉም ሳንለቅ ለአማርኛ ተናጋሪዎች የሚገባና የአማርኛን ቋንቋ ስልት የተከተለ አድርገን
ካልተረጎምነው ለሚያነቡት ሰዎች ግልጽ አይሆንም። ማለት ነው።
ከዚህ ቀጥለን በእግዚአብሔር፤
በአዳም እና በሔዋን መካከል
የተደረገውን ውይይት እና በእባብም ላይ ጭምር የተነገሩትን ርግማኖች እንሰማለን። በዚህ ጽሁፍ ላይ የገለጽኳቸው በዘፍጥረት መጽሐፍ
በምዕራፍ 3 ከቁጥር 9 ጀምሮ እስከ 17 የተገለጹትን ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ሳይሆን አሳጥሬ ለመከታተል የሚያመች አድርጌ ነው ያቀረብኩት
ሙሉውን ማየት ከፈለጋችሁ የግእዙን መጽሐፍ ቅዱስ መመልከት ትችላላችሁ።
አንድ ትኩረት ልታደርጉበት የሚገባችሁ ነገር ቢኖር “የቃል
በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም” በቅደም ተከተላቸው በሚለው ትርጉም ስር ትርጉማቸውን የምገልጸው
ከመስማት አልፋችሁ ተጨማሪ ምርምርን ወይም ፍለጋን በሚጠይቅ መልኩ ነው ።
ለምሳሌ፦ “አይቴ ሀሎከ አዳም?”
የሚለውን ዐረፍተ ነገር ወይም ጥያቄ የምተረጉመው
·
አይቴ=የት
·
ሀሎከ= አለህ(ነህ)
·
አዳም=ሰም ወይም በቁሙ አዳም ማለት ነው እያልኩ
ሳይሆን
·
የት
·
አለህ(ነህ)
·
በቁሙ(አዳም)
በማለት በዚህ መልኩ ነው።
ስለዚህ
“አለህ ወይም ነህ” የሚለው የአማርኛ ትርጉም የሚናገረው ስለየትኛው የግእዝ ቃል ነው? የሚለውን ለማወቅ የምትጠቀሙት መንገድ በቅደም
ተከተሉ ብቻ ነው። ለምሳሌ ነህ የሚለው በ2ኛ ተራቁጥር(ቁጥርም ባይኖር ቅደም
ተከተሉን ስናይ ማለት ነው) ስለሆነ ከግእዙ ዐ/ነገር በ2ኛ ተራቁጥር
ላይ የሚገኘው “ሀሎከ” የሚለው ቃል ስለሆነ ነህ የሚለው ትርጉም የ”ሀሎከ” ነው ማለት
ነው።
ለጊዜው ትርጉም የማይሰጥና ግራ የሚያጋባ መስሎ ሊታያችሁ ይችላል የተወሰነ
ጥረት ካደረጋችሁ በኋላ ግን ይገባችኋል እውቀትም የበለጠ ትጨምራላችሁ። ስለዚህ አሁን ቀጥታ ወደ ዋናው ክፍል በመግባት መተርጎም
እንጀምራለን።
እግዚአብሔር፣ አዳም፤ ሔዋን፤ እና እባብ እግዚአብሔር ይቤሎ ለአዳም፡= እግዚአብሔር አዳምን አለው
“.. አይቴ ሀሎከ አዳም.. ?
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
የት፤ አለህ (ነህ) ፤ አዳም (በቁሙ ስም)
የዐረፍተ ነገር
እና የይዘት ትርጉም፦
“አዳም ሆይ የትነህ”? “ሆይ” የሚለው ቃል በዐረፍተነገሩ ላይ ባይኖርም ለቅርብ ወይም ለሁለተኛ መደብ
የምንጠቀመው ተጨማሪ የቋንቋ ውበት ነው።
አዳም ይቤሎ ለእግዚአብሔር፡=አዳም እግዚአብሔርን አለው
“.. ሰማዕኩ ቃለከ እንዘ ታንሶሱ ውስተ ገነት
ወፈራህኩ እስመ ዕራቅየ አነ ወተኀባእኩ.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ሰማሁ፤ ቃልህን፤ ስ፤ስትመላለስ፤ ውስጥ፤ ገነት፤
ፈራሁም፤ ሰለ፤(እና) እራቁቴን፤ እኔ፤ ተሸሸግሁ፤
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
“በገነት ውስጥ ስትመላለስ
ሰማሁ፤ እራቁቴን ስለሆንኩም ፍራሁና ተደበቅሁ ወይም (ተሸሸግሁ)
እግዚአብሔር ይቤሎ ለአዳም፡=እግዚአብሔር አዳምን አለው
“.. መኑ አይድዐከ ከመ ዕራቅከ አንተ እም ዕፅኑ
ዘአዘዝኩከ ከመ ኢትብላዕ እምኔሁ በላእከ?.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ማን፤ ነገረህ፤ እንደ፤ እራቁትህን፤ አንተ (በቁሙ)፤ተክል፤(እንጨት፤ዛፍ፤)
የ፤ ያዘዝኩህን፤ እንደ እንዳትበላ፤ ከሱ፤ በላህን?
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
እራቁትህን መሆንህን ማን ነገረህ? እንዳትበላ ካዘዝኩህ ከዚያ ፍሬ በላህን?
አዳም ይቤሎ ለእግዚአብሔር፡= አዳም እግዚአብሔርን አለው
“.. ብዕሲት እንተ ወሀብከኒ ምስሌየ ትንበር
ይእቲ ወሀበተኒ ወበላእኩ-” *”ዘ” ስለሚለው አገባብ በሌላ ክፍል እንማረዋለን።
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ሴት፤ አንተ(በቁሙ) የሰጠኸኝ፤ ከእኔጋር፤ ትኖርዘንድ፤
እሷ፤ ሰጠቺኝ፤ ም፤ በላሁ(በላሁም)
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ከእኔ ጋር ትኖር ዘንድ የሰጠኸኝ ሴት እሷ ሰጠቺኝና በላሁ(ሰጠቺኝ በላሁም)
እግዚአብሔር ይቤላ ለሔዋን፡=እግዚአብሔር ሔዋንን አላት
“.. ለምንት ገበርኪ ዘንተ?.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ለምን፤ አደረግሽ ፤ ይህንን
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ለምን ይህንን አደረግሽ?
ብእሲት (ሔዋን) ትቤሎ ለእግዚአብሔር፡=ሔዋን (ሴትዮዋ)
እግዚአብሔርን አለችው
“.. አርዌ ምድር አስፈጠተኒ ወበላእኩ.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
አውሬ(እባብ) ምድር(መሬት) አሳሳተቺኝ፤ ም፤
በላሁ(በላሁም)
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
የምድር አውሬ(እባብ) አሳሳተቺኝ በላሁም፡
እግዚአብሔር ይቤሎ ለአርዌ ምድር፡=እግዚአብሔር እባብን(የምድር
አውሬን) አለው
“.. እስመ ገበርኮ ለዝንቱ ግብር ርጉመ ኩን
እምኵሉ እንስሳ ወእምኵሉ አራዊተ ምድር ወበ እንግድዓከ ሑር ወመሬተ ብላዕ..”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
እና(ስለ)፤ አደረግኸው፤ ይህንን፤ ሥራ፤ የተረገምክ፤
ሁን፤ ከ፤ ሁሉ(ከሁሉ)፤ እንስሳ፤ ም፤ከ፤ሁሉ(ከሁሉም) አውሬዎች፤ የምድር፤ በ፤ በደረትህ(በሆድህ) ሂድ፤ ም፤ መሬትን፤ ብላ፤
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ይህንን ሥራ ሠርተተኸዋልና ከእንስሳት ሁሉ፤ ከምድር አራዊት ሁሉ (ተለይተህ) የተረገምክ
ሁን፤ በሆድህም(በደረትህም) ሂድ፤ አፈርንም ብላ..
እግዚአብሔር ይቤላ ለሔዋን(ለብእሲት)፡= እግዚአብሔር
ሔዋንን(ሴትዮዋን) አላት
“.. አብዝኆ(ብዙኃ) አበዝኆ ለኀዘንኪ ወለሥቃይኪ
ወበጻዕር ለዲ..”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ማብዛትን፤ አበዛዋለሁ፤ኃዘንሺን፤ ም፤ ሥቃይሺን፤
በጭንቅም፤ ውለጂ
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ኃዘንሺንና ስቃይሺን አበዛዋለሁ በጭንቅም ትወልጃለሽ፤(ውለጂ)
እግዚአብሔር ይቤሎ ለአዳም፡=እግዚአብሔር አዳምን አለው
“.. እስመ ሰማዕከ ቃለ ብእሲትከ ወበላዕከ እም
ውእቱ ዕፅ ባሕቲቱ ዘአዘዝኩከ ከመ ኢትብላዕ ርግምተ ትኩን ምድር…”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
እና፤ ሰማህ፤ ቃልን፤ ሚስትህ፤ በላህም፤ ከ፤
እሱ፤ ተክል(ፍሬ) ብቻውን፤ የ፤አዘዝኩህን፤ እንደ፤ አትብላ፤ የተረገመች፤ ትሁን፤ ምድር(መሬት)
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
የሚስትህን ቃል ሰምተህ እንዳትበላ ካዘዝኩህ ከዚያ ተክል(ፍሬ) በልተሃልና መሬት በአንተ
ምክንያት የተረገመች ትሁን(ከአንተ የተነሣ)
No comments:
Post a Comment