የጭንቅ
ሰቆቃ
ሰቆቃ
አንተ ቸር ፈጣሪ አልፋና ዖሜጋ
ሰላም የባሕርይህ ይቅርታም ካንተ ጋ
ነውና ወደ እኛ ቀኝ እጅህን ዘርጋ፤
ሰብሳቢ የሌለው የባዘነ መንጋ
ሆነን በሜዳ ላይ ቀርበናል ላደጋ።
የኃያላን አምላክ የነገሥታት ጌታ
ፈጥነህ ድረስልን እንዳንንገላታ፤
ልባችን ኮብልሎ ከአንተ ሸፍተን
ብዙ ተንገላታን ለረጅም ዘመን፤
የጥበብ ባለቤት መሆንህን ዘንግተን
በምድራዊው እውቀት ስንመካ ቆየን፤
በታንክ በመትረየስ ስናምን በይፋ
እየከዳን ሄደ እየጣለን ጠፋ፤
ያመኑት ሲከዳ ዋ! ታላቅ አበሣ
ወዳጅ ጠላት ሆኖም ሊበላን ተነሣ።
ተጣላን፣ ተብላላን፣ ተገዳደልንሣ!
ምነው አእምሮ አጣን ሆን እንደ እንስሣ! ።
ኀያሉ ፈጣሪ የሰላሙ ጌታ
ኢትዮጵያን ታደጋት ሁንላት መከታ
ወዳንተ እየጮኸች ቃሏን አሰምታ
ማረኝ ትልሃለች እጆቿን ዘርግታ
ዕንባን እያነባች ጸሎቷን ሳትገታ
ደምን ታለቅሳለች ከጧት እስከማታ።
የዘረኞች ክፋት የክፉዎችም ኃል
ከቦ ሲያጣድፋት ሲጎዳት በከፊል
አምላክ ሆይ ገላግላት የምጥ ጣር ይዟታል።
ፈጣሪ በሰጠሽ በቃል ኪዳንሽ
አመጸኛውን ሰው ስምኦንን ያዳንሽ
በዚያው ታላቅ ፀጋሽ በጽኑ ምልጃሽ
ዛሬም በዚህ ዘመን ማልደሽ ልጅሺን
አድኛት ታደጊያት እናት ኢትዮጵያን።
እምዬ ኢትዮጵያ ውቢቷ ሐገሬ
ዘመን ጣለሺና ጠወለግሽ ዛሬ
በልጆችሽ ኀዘን ኑሮሽ ስለከፋ
መልክሽ ተለውጦ ውበትሺም ጠፋ።
በአንበሦች ጉድጓድ እንደሚል መጽሐፍ
ዳንኤልን ያዳንክ ሕይወቱ ሳያልፍ
ኢትዮጵያን አድናት፣ ታደጋት፣ ከገዳዮች ሰይፍ።
ፈጣሪ ሆይ እርዳት ስማት በጽሙና
እምዬ ኢትዮጵያ ተጨንቃ በጠና
ከሞት አፋፍ ሆና ትጣራለችና።
ኢትዮጵያ ተናዘዥ ኃጢአትሺን ንገሪ
ለሊቀ ካህናቱ ለዓለም ፈጣሪ፣
ንስሐ ከገባሽ ምንም ሳትሠውሪ
እርሱ ያድንሻል ነውና መሐሪ።
አምላክ ሆይ አድነን አውጣን ከፈተና
ሕግህን ተላልፈን በድለናልና።
ባደረገቺው ግፍ በሠራቺው ኃጢአት
ከእንግዲህ ፈርጀ ምድርን ላላጠፋት
ለቃል ኪዳን ማጽኛ ለውል ስምምነት
በእኛ መካከል ለእውነት ምልክት
ስየ አሳይሃለሁ ቀስቴን በደመና
ብለህ በነገርከው ለኖኅ በቅድምና
ፈጣሪሆይ ማረን መሐሪ ነህና።
ከፊቷ መትረየስ ከኋላዋ መድፍ
በስተቀኞ ታንክ በግራዋም ሰይፍ
ከበው ሲያስጨንቋት ኢትዮጵያን በሰልፍ
ፈርታ ተንቀጥቅጣ ደንግጣ ተዳክማ
ይኸው ታለቅሳለች መካከል ላይ ቆማ
እምዬ ኢትዮጵያ ባልቴቲቱ እማማ
ይኸው ታለቅሳለች መካከል ላይ ቆማ።
ስለ ዚህ ፈጣሪ ሳትጠፋ ፈጽማ
ፈጥነህ ታወጣት ዘንድ ከጥፋት አውድማ
ልቅሶዋን አዳምጥ ጩኸቷንም ስማ።
ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብ ብለህ
የማልክላቸውን ለጥንት ወዳጆችህ
ፈጣሪ ሆይ አስብ ጎብኘን በምህረትህ
አቤቱ አታጥፋን በደላችን ቆጥረህ።
ወንጌልን ለዓለም ዞረው ባበሠሩ
በማያምኑትም ፊት ሳይፈሩ ሳያፍሩ
ስምህን በይፋ ቆመው ባበሠሩ
በሐዋርያትህ ስም ማረን አንተ ቸሩ።
ኃጢአታችን በዝቶ ዕውን ቢሆን ዛሬ
ምድር ተለውጣ ሆነቺብን አውሬ።
በክፉ አሟሟት በከንቱ እንዳናልቅ
አቤቱ አምላካችን ፍጥረትህን ጠብቅ።
ማረን እራራልን አንተ አምላከ ሰላም
ልትከዳን ነውና ይህች የተውሶ ዓለም።
ወዳንተ እንጮሃለን በልቅሶ በዋይታ
የምሕረት ባለቤት ማረን አንተ ጌታ
አምላከ አብርሃም ወአምላከ ሣራ
አምላከ ኤልያስ ወአምላከ ዕዝራ
ኢትዮጵያን አደራ ኢትዮጵያን አደራ
እንለምንሃለን ልጆቿ በጋራ።
Its Good Thing Thank You!
ReplyDelete